ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በማን እና የት እንደታሰረ ማወቅ እንዳልተቻለ ጠበቃው ተናገሩ

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ያለበት ቦታ ሳይታወቅ ቀናት መቆጠራቸው እንዳሳሰባቸው ጠበቃው ተናገሩ።

እሁድ ሚያዚያ 23/2014 ዓ.ም. በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎ በቁጥጥር ሥር ውሏል የተባለውን የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ አድራሻን ማወቅ እንዳልተቻላቸው ጠበቃው አዲሱ አልጋው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃው እንዳሉት እሁድ ረፋድ ላይ የታጠቁ እና ሲቪል የለበሱ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጋዜጠኛው ተከራይቶ ወደ ሚኖርበት ጊቢ በአጥር ዘለው ከገቡ በኋላ 'ለጥያቄ ትፈለጋለህ' ብለው ደንበኛቸውን ይዘው መሄዳቸውን ተናግረዋል።

ጋዜጠኛው በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከዋለ 48 ሰዓታት ቢያልፉም እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረቡ እና ታስሮ የሚገኝበትን ቦታ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱ እንዳሳሰባቸው ጠበቃው ጨምረው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እስካሁን አድራሻው ያልታወቀው የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ መታሰር አሳሳቢ ነው ብለዋል።

ኮሚሸነር ዳንኤል ይህን ያሉት ዛሬ የተከበረውን የፕሬስ ነጻነት ቀንን በማስመልከት ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ ነው።

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከዚያም ደግሞ የኛ በሚባል ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ሲሰራ ነበር።

ጋዜጠኛ ጎበዜ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው በገቡ ወቅት በፌስቡክ ገጹ በሚያጋራቸው መረጃዎች የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር።

የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጠበቃ አቶ አዲሱ አልጋው፤ "እሁድ ሚያዚያ 23 ከረፋዱ 4 ሰዓት አካባቢ ተከራይቶ ወደሚኖርበት ግቢ የመንግሥት ፀጥታ ኃይል ነን የሚሉ በቁጥር 8 የሆኑ ሲቪል የለበሱ እና የታጠቁ በአጥር ዘለው ገብተው 'ለጥያቄ ትፈለጋለህ' ብለው ይዘውት ሄደዋል" በማለት የተፈጠረውን ያስረዳሉ።

ፖሊስ ጋዜጠኛውን ፍርድ ቤት ካቀረበው በሚል ዛሬ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ተገኝተው ቢጠባበቁም ጋዜጠኛ ጎበዜ ችሎት ፊት አልቀረበም በማለት ጠበቃው ይናገራሉ።

"ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስረኞች ክትትል ሄጄ ብጠይቅም ማግኘት አልቻልኩም። 'የለም' ነው የሚሉት። ቀጥሎ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ሄጄ ብጠይቅም እነርሱም 'እኛ ጋር የለም" አሉኝ" በማለት ጋዜጠኛው ታስሮ የሚገኝበትን ቦታ ለማወቅ ያደረጉትን ጥረት ያስረዳሉ።

"በከባድ ወንጀል የተጠረጠሩ ወይም እጅ ከፈንጅ የተያዙ ተጠርጣሪዎች ካልሆኑ በቀር በመርህ ደረጃ ፖሊስ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማንኛውም ሰው ማሰር አይችልም" ያሉት ጠበቃው፤ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የገባ ሰው ወደ ፍርድ ቤት የሚጓጓዝበትን ሰዓት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት በማለት የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት ዋቢ በማድረግ ጠበቃው ስለደንበኛቸው ተናግረዋል።

በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የገቡ ሰዎች ከጠበቆቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የመገናኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳላቸውም የጠቀሱት ጠበቃው፤ ደንበኛቸው ግን ይህን መብቱን መነፈጉን ይገልጻሉ።

ጠበቃው ከላይ የጠቀሷቸውን ታሳቢ በማድረግ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በእስር ላይ ሳለ፣ ከቤተሰብ እና ጠበቃ ጋር እንዳይገናኝ መደረጉ እና በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረቡ የሰብዓዊ መብት ጥስት ነው ይላሉ።

የጎበዜ ሲሳይ እስርን በተመለከተ ፖሊስ እስከ አሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።