ዓለም ዛሬም ያልረሳት አና ፍራንክ በናዚዎች ከተያዘች በኋላ ምን ደረሰባት?

በለጋ ዕድሜዋ ታሪክ የሠራችውና ዝናዋ በዓለም የናኘው አና ፍራንክ የተወለደችው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 12/1929 ነበር።

የሆሎካስት ጭፍጨፋ ጊዜ ኔዘርላንድስ ነበረች።

ከናዚ ወታደሮች ተደብቃ የጻፈችው የውሎ መዝገብ የታተመው ሕይወቷ በናዚ ካምፕ ውስጥ ካለፈ ከሰባት ዓመታት በኋላ ግንቦት 30/1952 ነው።

አና ያኔ ትኖርበት የነበረው ቤት ዛሬ ላይ የቱሪስት መዳረሻ ነው። ለሕዝብ ዕይታ ከተከፈተ ዘንድሮ 62ኛ ዓመቱን ይዟል።

ፕሪንሰንግራችት 263 የተባለው የቀድሞው የአና መኖሪያ በ1960ዎቹ ነበር ታድሶ ለቱሪስቶች ክፍት የተደረገው።

አና አምስተርዳም ውስጥ ከቤተሰቦቿ ጋር ትኖር ነበር። በ1942 ግን ከናዚ ወታደሮች መሸሸግ ግድ ሆነባቸው።

ናዚዎች አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ አይሁዳውያንን የማጥፋት እኩይ አላማ ይዘው ነበር የተነሱት።

አና ከእነዚህ ወታደሮች ተደብቃ የእለት ከእለት ውሎዋን ትጽፍ ነበር። ይህ ጽሑፍ በዓለማችን ገናና ስም ካተረፉ መጻሕፍት አንዱ ነው።

አና ልጅ ሳለች

አና ወይም በሙሉ ስሟ አናሊስ ማሪ ፍራንክ በጀርመን፣ ፍራንክፈርት ውስጥ ኤዲት እና ኦቶ ከተባሉ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ተወለደች።

ታላቅ እህቷ ማርጎት ሦስት ዓመት ትበልጣታለች።

ደራሲ የመሆን ሕልሟ እውን የሆነው ካለፈች በኋላ ነው።

በሆሎካስት በአሳዛኝ ሁኔታ ከተቀጠፉ አንዷ ናት።

አባቷ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ካለፉ በኋላ ነበር የልጃቸውን የውሎ ማስታወሻ ያሳተሙት።

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲገባደድ ጀርመን በድህነት ትማቅቅ ነበር።

የናዚ ፓርቲ መሪ አዶልፍ ሂትለር ለጀርመን ችግሮች ባጠቃላይ አይሁዳውያንን ተጠያቂ በማድረግ ይታወቃል።

ፓርቲው በ1933 ሥልጣን ሲጨብጥ፣ አይሁዳውያንን ማንገላታት ያዙ።

የአና ቤተሰቦች ደኅንነታችን ይጠበቃል ብለው ወደ ኔዘርላንድስ፣ አምስተርዳም ሸሹ።

አና ትምህርት ቤት ገባች። አዳዲስ ጓደኞች አፈራች። ደች ተማረች።

የ10 ዓመት ልጅ ሳለች፣ መስከረም1/1939 ጀርመን ፖላንድን ወረረች። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተነሳ።

ከአንድ ዓመት በኋላ ጀርመን ኔዘርላንድስን ወረረች። ናዚዎች አይሁዳውያንን ማሳደዱን ገፉበት።

አና በሆሎካስት መካከል

አና 13 ዓመት ሲሞላት የውሎ መዝገብ ተሰጣች። ኪቲ ብላ መዝገቡን ሰየመችው።

ለመጀመሪያ ጊዜ የጻፈችበት ሰኔ12/1942 ነበር።

ወቅቱ ናዚዎች በኔዘርላንድስ የሚኖሩ አይሁዳውያንን ያሳድዱ የነበረበት ነው።

የአና እህት ማርጎ ካምፕ ውስጥ እንድትሠራ በናዚ ታዘዘች።

ማርጎ በካምፑ የሚደርስባትን በመፍራት ቤተሰቡ የአባትየው ንግድ ቤት ጀርባ ለመሸሸግ ወሰነ።

የአና አባት ኦቶ መደበቂያቸውን ለሳምንታት ሲያዘጋጁ ነበር የቆዩት።

ከእነ አና ጋር ቫን ፔልስ የተባለው ቤተሰብ አራት አባላትም አብረዋቸው ተደብቀዋል።

የእነ አና ቤተሰብ ወዳጆች ምግብ ያቀብሏቸው ነበር። መረጃም ጭምር።

የአና ወዳጅ የውሎ መዝገቧ ነበር። ውሎዋን ትጽፋለች፣ ግጥም ትጽፋለች፣ ታሪኮች ትጽፋለች።

በአካባቢዋ ካለው አሰቃቂ እውነታ እራሷን የምታወጣው በጽሑፍ ነበር።

አንድ ቀን በኢንግላንድ ያለው የኔዘርላንድስ የትምህርት ሚኒስቴር በራድዮ ማስታወቂያ አስነገረ። ዜጎች በጦርነቱ ወቅት የተጻፉ የውሎ መዝገቦችን ጠብቀው እንዲያቆዩ።

ማስታወቂያውን የሰማችው አና የውሎ ማስታወሻዋን ወደ መጽሐፍ ለመቀየር ተነሳሳች።

Het Achterhuis ወይም The Secret Annex የተባለውን መጽሐፏን እያረቀቀች ሳለ ነው ናዚዎች ቤተሰቦቿ የተደበቁበትን መጠለያ ያገኙት።

ቤተሰቧ ለሁለት ዓመታት ከተደበቁ በኋላ ነበር የተያዙት። ናዚዎች መጠለያውን እንዴት እንደደረሱበት እስካሁን አይታወቅም።

ነሐሴ 4/1944 ተደብቀው የነበሩትን ሰዎች ወደ አውሽዊትዝ-ቢርካኑ የግዳጅ ማቆያ ከተቷቸው።

አና ለመጨረሻ ጊዜ በውሎ ማስታወሻዋ የጻፈችው ወደ ግዳጅ ማቆያው ከመወሰዳቸው ከሦስት ቀናት በፊት ነው።

አና ከተያዘች በኋላ ምን ገጠማት?

አና እና ቤተሰቧ ጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ ስለነበረ ወዲያውኑ በግዳጅ ማቆያው እንዲሠሩ ታዘዙ።

የአና አባት ከቤተሰቡ ተነጠለ። ከዚያም አና እና ማርጎት ከእናታቸው ተለያዩ።

አምስተርዳም ውስጥ ቤተሰቡ ተደብቆ ሳለ ምግብ ያቀብሉ የነበሩት የአና አባት ጓደኞች የአናን የውሎ ማስታወሻ አግኝተው ጠብቀው አቆዩት።

አና አንድ ቀን ተመልሳ ትመጣለች ብለው ነበር። ግን አልተመለሰችም።

ጥቅምት 1944 አና እና እህቷ ማርጎት ቤርገን-ቤልሰን ወደተባለው የግዳጅ ማቆያ ተላኩ። ጤናቸውም ይቃወስ ጀመር።

በ1945 በጥቂት ቀናት ልዩነት ሁለቱም በታይፈስ ሞቱ። እናታቸው ኤዲትም ተገደሉ።

ከቤተሰቡ መካከል ከሆሎካስት የተረፉት የአና አባት ብቻ ናቸው።

አምስተርዳም የነበሩ ወዳጆቻቸው የአናን የውሎ መዝገብ ሰጧቸው።

አና ከሞተች በኋላም በጽሑፏ ዘመናት ተሻግራ መኖር እንደምትሻ የተገነዘቡት አባት የልጃቸውን ጽሑፍ አሳተሙት።

ሰኔ 25/1947 ላይ ከ3,000 በላይ ቅጂ ታተመ።

ብዙም ሳይቆይ መጽሐፉ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተረጎመ። ተውኔትና ፊልምም ሆኗል።

የአናን ታሪክ በመላው ዓለም ሚሊዮኖች አንብበውታል።

ደራሲ የመሆን እና ከናዚ ተደብቃ ሳለች ስላሳለፈችው ሕይወት የሚገልጽ መጽሐፍ የማሳተም ሕልሟ እውን ሆኗል።

ከቤተሰቦቿ ጋር ተደብቀውበት የነበረው ቤትም በይፋ ለጎብኚዎች ተከፍቷል።

የውሎ ማስታወሻዋ ዋና ቅጂ የሚገኘው በዚህ ቤት ነው።