የጠቅላይ ሚኒስትሩ የባለፉት ስድስት ወራት የምጣኔ ሀብት ግምገማ

በባለፉት ስድስት ወራት 297 ቢሊዮን ብር ወጪ ባደረገችው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት መታየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት የካቲት 15፣ 2014 ዓ. ም በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት አፈጻጸም በተመለከተ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት።

በሦስተኛው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባሎች የቀረቡላቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሁለት ከፍለው ምላሽ ሰጥተዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች፣ በአፋር ክልል እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት፣ የእስረኞች መፈታት፣ ከህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር፣ የሻከረው ዲፕሎማሲ፣ የልዩ ኃይሎች መዋቅር እንዲሁም በአምባሳደሮች ሹመት ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።

በርካታ የምክር ቤቱ አባላት የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ ኤሌክትሪክ ማመንጨትን በተመለከተ ደስታቸውን በመግለፅ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ በአገሪቱ ውስጥ አነጋጋሪ የተባሉት የሁለቱ ጄኔራሎች ባጫ ደበሌና ሃሰን ኢብራሂም እንዲሁም ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በአምባሳደርነት ስልተሾሙበት መስፈርት ጥያቄዎች ተነስተዋል።

የጦርነት ኢኮኖሚ

ኢኮኖሚን በሚመለከት አገሪቷ አሁን ያለችበት ወቅት የጦርነት ጊዜ ኢኮኖሚ መሆኑንና በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉት በመግለፅ ነው ንግግራቸው የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ከጦርነቱም ጋር ተያይዞ ብድርና እርዳታ እንደ ልብ ባለመገኘቱ የታቀዱ የልማት ሥራዎችን በተፈለገው መንገድ ለማሳካት እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አመራሩ የሚያተኩረው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመሆኑ የልማት ሥራዎች ስለመስተጓጎላቸውም አስረድተዋል። "አመራር ያጣ ሥራ እንኳን በኛ አገር በሌሎቹም ላይ ውስንነት አለው" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ጦርነቱ በሚያስከትለው መፈናቀል፣ መገደል፣ መዘረፍ፣ መደፈርና ሌሎች በርካታ ጦሶች ሕዝቡ ስቃይ ላይ መሆኑንና አምራቹ ኃይልም ወደ ጦርነት መግባቱም የአገሪቷ ምጣኔ ሀብት ላይ ጫና አሳርፏል ብለዋል።

ከጦርነት በተጨማሪ ከፍተኛ ድርቅ መፈናቀሎችን እንዲሁም የሀብት ውድመትን በማስከተሉ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ተደራርበው የራሳቸውን ጥቁር ጠባሳ ማሳረፋቸውንም አክለዋል።

በተጨማሪም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት እንዲሁም የዓለምን ኢኮኖሚ ማዛባቱ፣ የዓለምን የንግድ ሥርዓት ማስተጓጎሉ በአገሪቱ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩም ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች ባሉበት ሁኔታ የአገሪቱን ስድስት ወራት የገመገሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፈተናዎች አንዳሉ ሆነው መልካም ዕድሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በርካታ አገራት አጠቃላይ የእንቅስቃሴ እቀባን ተከትለው በርካታ የአፍሪካ አገራት የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎችን በመግታታቸው ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ማስከተሉንና መንግሥታቸው የተሻለ አማራጭ የሚለውን በመውሰዱ ከዚህ መትረፉን አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሁኔታ "የዳቦ እጥረት ወይም ኮሮና ስለሚገድሉን እንቅስቃሴ አንገድብም" በሚል አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣ ማስክ ማድረግና ሌሎች እርምጃዎችን የመውሰድ ፖሊሲን ተከትላለች።

በዚህም በርካቶች የኮሮናቫይረስን እንዲለማመዱትና በተሻለ ሁኔታ እንዲዋጉት ከማድረግ ባሻገር በወጪ ንግድ፣ በቱሪዝምም ሆነ በግብርና ዘርፎች ላይ "በመከራ ላይ ዕድልን የፈጠርንበት" ወቅት ነው ይላሉ።

ባለፉ ስድስት ወራት ከፍተኛ ጫና በነበረው ሁኔታ መንግሥት ሊያስገባ ይዞት የነበረው ዕቅድ 185.8 ቢሊዮን ብር ቢሆንም መሰብሰብ የቻለው 171.3 ቢሊዮን ብር፣ ወይም 92 በመቶ ነው።

መንግሥት ከዕቅዱ 92 በመቶ መሰብሰብ ያስቻለው በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ ከነዚህም መካከል ግብር የሚሰበሰብት አካባቢ ችግር ውስጥ መሆኑን አውስተዋል።

ይህም ሆኖ ባለፈው ዓመት ስድስት ወር ከነበረው ገቢ በንፅፅር ሲታይ 14.9 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።

ገቢዋ ቢሻሻልም በአገሪቱ ከፍተኛ ወጪም የተመዘገበበት መንፈቅ ዓመት እንደሆነም ተገልጿል።

የአገሪቷ ወጪ ባለፉት ስድስት ወራት ሲታይ 297 ቢሊዮን ብር ሲሆን ከባለፈው ዓመት ስድስት ወራት ጋር ሲነፃፀር 39 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል።

በዚህም ሁኔታ ገቢው ቢጨምርም ወጪው 39 በመቶ በመሆኑ የበጀት ጉድለቱ መስፋቱንና ይህንንም ሚዛን ለመጠበቅ የማክሮ እርማት ማስተካከያዎች ካልተሰሩ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ጉዞውን አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ወጪ መቀነስ፣ ወጪ መቆጠብና ሊቀሩ የሚችሉ ሥራዎችን መተውና በተቻለ መጠን ለገቢው የቀረበ የአወጣጥ ሥርዓት መከተል ያስፈልጋልም ተብሏል።

የውጭ ገበያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት 6 ወራት የነበረውን የአገሪቱውን የውጭ ገበያ እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ ያስገባችውን ምርት በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባለፈው 6 ወር የአገሪቱ የውጭ ገበያ 25% ማደጉን ገልጸዋል።

"ዘንድሮ 4 ቢሊዮን ብር የውጭ ገቢ አስገብተናል። በሁለት ዓመታት አንድ ቢሊዮን ብር ጨምሯል ማለት ነው" ሲሉ ካለፈው ዓመት አነፃፅረዋል።።

የኢትዮጵያ በዋነኛነት ወደ ውጭ የላከችው ቡና፣ ጫት፣ አበባ እና ቅባት እህል እንደሆነና ዘርፉ በ21% እንዳደገም አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የአገሪቱ የአገልግሎት ዘርፍ 27% ማደጉን ተናግረዋል።

"ዘንድሮ ወደ አገር ውስጥ ያስገባነው በ6 ወር 25% አድጓል። ከውጭ የሚገባው ሲጨምር ወደ ውጭ ተልኮ የሚገኘውን ይቀንሳል" ሲሉም ወደ አገር ውስጥ የሚገባው እንዲቀንስ አሳስበዋል።

ዘንድሮ ከምግብ በተጨማሪ በዋነኛነት ማዳበሪያ እና ነዳጅ ከውጭ ማስገባቷል ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ከውጭ ይገባ የነበረ ምርትን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ የረሻሉ ሆነው ከተገኙት መካከል ብቅል፣ ፋርማሱቲካል ምርቶች፣ ቴክስታይል፣ ጫማ፣ ዳይፐር እና የሲሚንቶ ግብዓት የሆነውን ኮል ጠቅሰዋል።

ባንክና ፋይናንስ

የባንኮች አጠቃላይ ሀብት ከ1.8 ትሪሊዮን ብር ወደ 2 ትሪሊዮን ብር እንዳደገ ጠቅሰው "የአገር ውስጥ ባንኮች ለውጭ አገር ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገበያ መግባት መዘጋጀት አለባቸው" ብለዋል።

ላለፉት 20 ዓመታት የአገር ውስጥ የግል እንዲሁም የመንግሥት ባንኮች ያለ ውጭ አገር ባንኮች ውድድር እንደቆዩ ጠቅሰው፤ ከዚህ በኋላ ግን የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገበያው የሚገቡበት የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ባለፉት 6 ወራት የባንክ ቅርንጫፎች ቁጥር ወደ 7400 ከፍ እንዳለ እና የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ከ1.35 ትሪሊዮን ብር ወደ 1.5 ትሪሊዮን ብር ማደጉን ጠቅሰዋል።

በብድር ረገድ በአጠቃላይ 147 ቢሊዮን ብር ብድር የተሰጠ ሲሆን ከዚህ መካከል፤ 70 ቢሊዮን ብር ለአገልግሎት ዘርፍ፣ 50 ቢሊዮን ብር ለኢንዱስትሪ እና 28 ቢሊዮን ብር ለግብርና ውሏል።

"ለግል ዘርፍ የሚሰጠው ብድር እንዲያድግ ተወስኗል። ስለዚህም 69% ብድር የተሰጠው ለግሉ ዘርፍ ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ግብርና

ባለፈው ክረምት 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን ዕቅዱን ያሳካና 336 ሚሊዮን ኩንታል ምርትም የተሰበሰበት ነው ብለዋል።

ባለፈው ክረምት መንግሥት የግብርና ዕቅዱን አሳክቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዘንድሮው በጋ አምና የተጀመረውን የበጋ ስንዴ ምርት በሁለት ዙሮች ስድስት መቶ ሺህ ሄክታር ገደማ ማሳ በስንዴ እርሻ ለመሸፈን ሙከራ ተደርጎ፣ ወደ 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በበጋ እርሻ እንደሚመረት ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው ስንዴ 19 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ስንዴ ሲሆን ከውጭ የሚገባውንም ስንዴ ይተካዋልም ተብሎ ይጠበቃል።

ይህም አገሪቷ ራሷን በምግብ ለመቻል ከምታደርገው ጥረት ጋር ተያይዞ ስኬታማ እንዲሆን የሚያስችል ሲሆን ሙሉ በሙሉም ይህንንም ለማሳከት ኩታ ገጠም አስተራረሶችን ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።

ኩታ ገጠም አስተራረሶች መካናይዝድ እርሻ ለመጀመር፣ ፓምፕና መስኖ ለመጠቀምና የአርሶ አደሮችን ጉልበት ለመቀነስ ከማስቻሉም በላይ የስንዴ ምርትን በመጨመር ውጤታማ መሆኑን ያሳየ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

አገሪቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እንዲሰፉ ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ ማዳበሪያ ሲሆን ባለፈው ዓመት አገሪቱ ለማዳበሪያ ያወጣችው 500 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ግን 1.1 ቢሊዮን ብር መውጣቱን ተናግረዋል።

ለዚህም የዋጋ ግሸበቱ አንዱ ምክንያት ሲሆን ወጪውንም ከፍ እንዲል አድርጎታል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ዙሪያ አሉታዊ ዜናዎች ቢሰራጬም፤ 1.63 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ገብቷል። ይህም አምና ከነበረው ስድስት ወር አንፃር 23 በመቶ እድገት አሳይቷል ብለዋል።

"በግራ እጃቸው ችግር አለ፣ ሰላም የለም ቢሉም በቀኝ እጃቸው ደግሞ ኢንቨስት ያደርጋሉ ማለት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩ በሚነገረው ልክ እንዳልሆነም ማሳያ ነው ይላሉ።

ሆኖም ኢትዮጵያ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅሟ ከፍተኛ እንደሆነና እስከ አርባ ቢሊዮን ቢመጣ መሸከም እንደምትችልም አፅንኦት ሰጥተዋል።

በኃይል (ኢነርጂ) ዘርፍ ብቻ በቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማስደረግ የሚያስችልም እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

"የአገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴም እንደተገመተው ዝቅ ያለ ሳይሆን ከ200 ሺህ ሰዎች በላይ በባለፉት ስድስት ወራት ንግድ ፈቃድ አውጥተዋል። ይህም ከአምናው አስር በመቶ ያደገ ነው" ብለዋል።

አዲስ ያወጡት ብቻ ሳይሆን የንግድ ፈቃድ ያደሱትም ጭማሬ ያሳየ ሲሆን፤ በባለፉት ስድስት ወራት 800 ሺህ ሰዎች ንግድ ፈቃዳቸውን አድሰዋል።

ለአገሪቱ ትልቁ ፈተናና የኢኮኖሚው ስብራት የሆነው ግሽበት ነው ሲሉም አክለዋል።

የኑሮ ውድነት

መንግሥት የኑሮ ውድነትነትን ለማርገብ ሲል ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ለነዳጅ ቢደጉሙም የነዳጅ ምርትን አገር ውስጥ ከማሰራጨት ይልቅ ወደ አጎራባች አገሮች የሚሸጡ መኖራቸውን እንደ መሰናክል ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የምግብ ምርትን ከገጠር ወደ ከተማ ለማምጣት የእሑድ ገበያ እንደተጀመረና የከተማ እርሻም እንደሚበረታታ ተናግረዋል።

የምግብ ሸቀጥ ተደራሽነትን ማስፋትን በተመለከተ "ሁሉም ሚኒስርት በየጓሮው እንዲያርስ እና በአካበቢው ለሚኖር ሰው በ1 እና 2 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ እዳ

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርቷ (ጂዲፕ) መካከል ብድሯ ከ58% በላይ እንደነበር ጠቅሰው ባለፉት 3 ዓመታት ግን ወደ 50% ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።

የውጭ ብድር ወደ 26% እንደቀነሰ እና የብድር ጫና በ22.4% እንደቀነሰ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተናገሩት።

"ሳይከፈል ያለፈ እዳ የለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገንዘብ ኖት መለወጡን ጨምሮ ሌሎችም የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች መደረጋቸው ለዘርፉ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጠቅሰዋል።

ኢንዱስትሪና ቱሪዝም

በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 177 የኢንዱስትሪ ሼዶች 158ቱ ለግል ባለ ሀብት እንደተሰጡና 104 ሼዶች ሙሉ በሙሉ ሥራ እንደጀመሩ ጠቅሰዋል። ይህም ከአምናው አንጻር የ16% እድገት የታየበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስመጣውን ምርት በአገር ውስጥ መተካት ላይ እንድታተኩርም በአጽንኦት ተናግረዋል።

ቱሪዝምን በተመለከተ ለመጪው ረመዳን ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ገብተው ዒድን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ጎርጎራ መስከረም ላይ ሥራ እንደሚጀምር አክለዋል።

ከሕዝብ ተወካዮች ስለ አብጃታ እና ሻላ ሐይቆች ልማት ለቀረበላቸው ጥያቄ "የጀመርነውን ስጨርስ እናስበብበታለን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ለመዳረሻ ልማት እንቅፋት የሆነው የታጣቂዎች ዝርፊያ እና የካሳ ጥያቄ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በተለይም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት ባለፉት 2 ሳምንታት ብቻ አምስት ወታደሮች እንደተገደሉና በአካቢው የሠራተኞች ግድያ እና ፈንጅ ቀበራ እንዲሁም ዝርፊያ ሥራ እንደሚያስተጓጉል ተናግረዋል።