ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከጉሊት እስከ ቅንጡ ሆቴል ግብይትን ያሳለጠው ኤም-ፔሳ ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል?
ከሁለት ወራት በኋላ በኢትዮጵያ ሥራ እንደሚጀምር ያስታወቀው ሳፋሪኮም፤ ኤም-ፔሳ የተባለውን የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት በአገሪቱ እንዲዘረጋ መንግሥት ፍላጎት እንዳለው ተዘግቧል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝን ጠቅሰው የአገር ውስጥ እና የኬንያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሳፋሪኮም ኤም-ፔሳን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲጀምር ይፈልጋል።
ከዚህ ቀደም መንግሥት የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓትን ለውጭ አገራት ኩባንያዎች ክፍት እንደማያደርግ መግለጹ አይዘነጋም።
አሁን ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሳፋሪኮም የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት ኤም-ፔሳ ፈቃድ እንዲሰጥ የሚያስችል ሕጋዊ አሠራር እየተነደፈ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ሚኒስትር ዴኤታውን ያጣቀሱ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፤ ሳፋሪኮም ለኤም-ፔሳ የፊታችን ግንቦት ፈቃድ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም ባወጣው የቴሌኮም ጨረታ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት ዝርጋታ አልተካተተም ነበር።
በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው እና የኢትዮ-ቴሌኮምን ጨረታ ያሸነፈው ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ ጥምረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ የተገኙት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያ ገበያውን ለኤም-ፔሳ ክፍት እንድታደርግ በተዘዋዋሪ መጠቆማቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለተኛውን የቴሌኮም ጨረታ ላልተወሰነ ጊዜ ቢያራዝመውም፤ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት ዝርጋታን ከዝርዝሩ እንዳስወጣው ተገልጿል።
ሳፋሪኮም ይህንን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ፈቃድ በቅርቡ እንደሚሰጠውም ታክሏል።
ኤም-ፔሳ የሚሠራው እንዴት ነው?
ኤም-ፔሳ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት ነው።
መሥራቹ የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ሲሆን፤ አሁን ላይ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየተተገበረ ይገኛል።
ኤም-ፔሳ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ከተጫነ በኋላ ገንዘብ ማስቀመጥ፣ ገንዘብ መቀበል፣ ክፍያ መፈጸም፣ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብን ወደ ስልክ ማዘዋወር፣ ገንዘብ ለሌላ ኤም-ፔሳ ተጠቃሚ መላክ እና ሌላም የገንዘብ ልውውጥ ማካሄድ ይቻላል።
እአአ በ2007 በሳፋሪኮም እና ቮዳፎን የተጀመረው ኤም-ፔሳ ኬንያ ውስጥ የሚተዳደረው በኬንያ ብሔራዊ ባንክ ነው።
ኤም-ፔሳ የሚለው መጠሪያ ውስጥ ኤም ሞባይልን ሲወክል፣ ፔሳ ደግሞ በስዋሂሊ ገንዘብ ማለት ነው።
የገንዘብ ልውውጥን የሚያሳልጡ የሳፋሪኮም ተወካዮች በተለያዩ መደብሮች ይገኛሉ። ለእነዚህ ተወካዮች ጥሬ ገንዘብ በመስጠት ወደ ኤም-ፔሳ ገንዘቡን እንዲያዘዋውሩ ማድረግ ይቻላል።
በኤም-ፔሳ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ያለ ገንዘብን በጥሬ ገንዘብ ከተወካዮቹ የመውሰድ አማራጭም አለ።
በተለይ ኬንያ ውስጥ ከጉሊት አንስቶ እስከ ቅንጡ ሆቴሎች ድረስ ክፍያ የሚፈጸመው በኤም-ፔሳ ነው።
አገልግሎቱ በሚገኝባቸው ሌሎች አገራትም የውሃ እና መብራት ክፍያን ጨምሮ ለምርት እንዲሁም ለአገልግሎት ክፍያ ለመፈጸም ሁነኛ አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል።
በኤም-ፔሳ የገንዘብ ልውውጥ ሲደረግ ወይም ከሳፋሪኮም ተወካይ ገንዘብ ሲወሰድ በገንዘቡ ልክ የሚወሰን የአገልግሎት ክፍያ ይጠየቃል።
ኤም-ፔሳን የትኞቹ አገራት ይጠቀማሉ?
ወደ ዲጂታል የገንዘብ ልውውጥ እየተሻገረ ባለው ዓለም ውስጥ ከፍተኛ እውቅና ካተረፉ ተሞክሮዎች አንዱ ኤም-ፔሳ ነው።
እአአ በ2010 በታዳጊ አገራት እጅግ ስኬታማው የሞባይል ገንዘብ መለዋወጫ ተብሎ ተሞካሽቷል።
ከኬንያ አልፎ በታንዛንያ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በግብፅ፣ በጋና፣ በሌሴቶ እና በሞዛምቢክ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የሳፋሪኮም ድረ ገጽ ይጠቁማል።
ጀርመን፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ቻይና ወዳሉ ባንኮች ገንዘብ ማዘዋወር ይቻላል።
የቮዳፎን ድረ ገጽ እንደሚለው ኤም-ፔሳ ከ50 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች አሉት።
ከአፍሪካ ትልቁ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት እንደሆነ የሚነገርለት ኤም-ፔሳ፤ የባንክ ደብተር ላላቸው ብቻ ሳይሆን የባንክ ተጠቃሚ ላልሆኑ ሰዎችም አገልግሎት በመስጠት ይታወቃል።
በተለይም የባንክ አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ኤም-ፔሳ ተደራሽ መሆኑ ለንግድ ብቻ ሳይሆን ለገንዘብ ቁጠባም መንገድ እንደከፈተ ይገለጻል።
ከገጠር እስከ ከተማ ጥሬ ገንዘብ ይለዋወጥ የነበረን ማኅበረሰብ ወደ ስልክ የገንዘብ ዝውውር በስኬታማ ሁኔታ እንዳሻገረ ይነገርለታል።
ኤም-ፔሳ ጥቃቅን እና አነስተኛ ነጋዴዎችን የሚያበረታታ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት እንደሆነ የሳፋሪኮም ገጽ ይጠቁማል።
ከተንቀሳቃሽ ስልክ የአየር ሰዓት ግዥ አንስቶ በተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያዘዋውራል።
ገንዘብ ለመቆጠብ እና ገንዘብ ለመበደር ኤም-ሸዋሪ የተባለ አዲስ አሠራርም ለተጠቃሚዎቹ ዘርግቷል።
የቮዳፎን ድረ ገጽ እንደሚጠቁመው፤ ኤም-ፔሳ እንደ ዌስተርን ዩኒየን፣ መኒግራም፣ ወርልድሬሚት፣ ሬሚትሊ እና ኤምኤፍኤስ አፍሪካ ያሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ መለዋወጫዎች ጋር ትስስር ፈጥሯል።
በየዓመቱ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከውጭ አገራት የሚነሳ የገንዘብ ዝውውር (remittance) ያስገኛል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ የገንዘብ ልውውጥ ዲጂታል ቅርጽ ሲይዝ ተደራሽነቱ ይሰፋል፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ያማለከም ይሆናል።
ኤም-ፔሳ እና ኤም-ብር ምን ያመሳስላቸዋል?
ኤም-ብር ኢትዮጵያ ውስጥ ተንቀሳቃሽ ስልክን የተመረኮዘ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት ነው።
በኤም-ብር ተጠቃሚዎች መካከል ገንዘብ ለማስተላለፍ፣ በኤም-ብር ተወካይ በኩል ጥሬ ገንዘብን ወደ ስልክ ለመውሰድ ወይም ከስልክ ተቀማጭ ጥሬ ገንዘብ ለማውጣትም ይውላል።
የተንቀሳቃሽ ስልክ የአየር ሰዓት መግዛትን ጨምሮ ውሃ እና መብራት ለመክፈል እንዲሁም ለሌሎችም የምርት እና የአገልግሎት ግዢዎች ኤም-ብርን መጠቀም ይቻላል።
ኤም-ፔሳ እና ኤም-ብርን ጨምሮ ሌሎች ዓለም ላይ ያሉ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓቶች መሠረታዊ ሐሳባቸው ተመሳሳይ ቢሆንም በአገልግሎት ዓይነት እና ቅልጥፍና ይለያያሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮ-ቴሌኮምን ድርሻ ለተለያዩ የቴሌኮም ኩባንያዎች ግዥ ክፍት ሲያደርግ ከተነሱ ነጥቦች አንዱ፤ የውጭ ቴሌኮሞች ወደ ኢትዮጵያ መግባት በዘርፉ ውድድር በመፍጠር የአገልግሎት ጥራትን ያስጠብቃል የሚለው ነው።
ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን በተለያዩ አገራት የተፈተሸ የሥራ ልምድ ያላቸው ተቋሞችን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ማስገባትን በአወንታዊ ጎኑ የወሰዱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሉ።
ኤም-ፔሳ ኢትዮጵያን ያሰጋል?
ኤም-ፔሳ የኢትዮ-ቴሌኮምን ጨረታ ያሸነፈው ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ ጥምረት በሚመራው ሳፋሪኮም ከሚሰጡ የቴሌኮም አገልግሎቶች አንዱ ነው።
ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕን የያዘው ጥምረት 850 ሚሊዮን ዶላር አቅርቦ ነበር ጨረታውን ያሸነፈው።
በመንግሥት የሚተዳደሩ እንደ ኢትዮ-ቴሌኮም ያሉ ተቋሞችን ለውጭ ኩባንያዎች ወይም የግል ባለሀብቶች የመክፈት ሐሳብ ደጋፊዎች እንዳሉት ሁሉ ነቃፊዎችም አያጣም።
ለመንግሥት ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ የሚያስገኙ ድርጅቶችን ለሽያጭ ማቅረብ መንግሥት የሚያገኘውን ትርፍ እንደሚቀንስ እንዲሁም በአገር ውስጥ የገበያ ተወዳዳሪዎች ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድርም የሚከራከሩ ይጠቀሳሉ።
ለውጭ ኩባንያዎች ሁሉንም ዘርፎች ክፍት ከማድረግ ይልቅ እንደ ፋይናንስ ያዙ ዘርፎች በማዕከላዊ መንግሥት ሥር ሆነው እንዲዘልቁ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው የሚል አስተያየት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይሰነዝራሉ።
እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ተቋሞች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት ቢሰጡም፤ እንደ ኤም-ፔሳ ባለ አገልግሎት የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የመግባታቸውን ጉዳይ በጥያቄ ምልክት የሚያስተናግዱት አሉ።
ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍን ለግል ባለሀብቶች ከከፈቱ የመጨረሻዎቹ አገራት አንዷ እንደሆነች ይነገራል።
በሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት፤ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና የዜጎችን ሕይወት በበጎ እንደሚቀይር በምሥረታው ወቅት አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በመታገዝ ከያዘችው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች መካከል የቴሌኮምን ድርሻ መሸጥ እንደሚገኝበት ገልጻለች።