በኒው ዮርክ የመኖርያ አፓርትመንት በተነሳ እሳት ሕጻናትን ጨምሮ 19 ሰዎች ሞቱ

በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ከተማ በሚገኝ አንድ የመኖርያ አፓርትመንት በተነሳ እሳት 19 ነዋሪዎች ሞቱ። ከሟቹቹ መካከል ዘጠኙ ሕጻናት ናቸው።

ሌሎች 32 ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብለዋል የኒው ዮርክ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ።

የእሳት አደጋ ክፍል ኮሚሽነር ዳኔል ኒጌሮ ለጋዜጠኞች እንዳሉት ከሆነ 19 ወለል ባለው የመኖርያ አፓርትመንት በየወለሉ ይነስም ይብዛ ተጎጂዎችን አግኝተናል፤ የተነሳው ጭስ ታይቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል።

ኤንቢሲ ዜና እንዳለው ደግሞ ይህ እሳት አደጋ ያስከተለው ሞት በኒው ዮርክ የ30 ዓመት ታሪክ አደገኛ የሚባለው ነው።

ይህ የእሳት አደጋ የተከሰተው በፊላደልፊያ በተመሳሳይ በመኖርያ አፓርትመንት በተነሳ ሌላ እሳት 12 ሰዎች መሞታቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

ከ12ቱ ሟቾች ስምንቱ ሕጻናት መሆናቸው ደግሞ ሐዘኑን የከፋ አድርጎት ነበር።

ትናንት እሑድ ብሮንክስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አፓርትመንት ላይ የተነሳው እሳት በአገሬው አቆጣጠር ከጠዋቱ 5 ሰዓት ገደማ የተቀሰቀሰ ሲሆን እሳት ከ2ኛ ወይም 3ኛ ወለል ላይ መነሳቱ ተነግሯል።

እሳቱ የተነሳበት ወለል በር ክፍት ስለነበረ ጭሱ ወደ ሌሎች ወለሎች ለመዛመት ጊዜ አልወሰደበትም ብለዋል ኮሚሽነሩ።

በዚያ አፓርትመንት በቅርብ የሚኖር ጆርጅ ኪንግ የተባለ የዐይን እማኝ ለኤፍፒ እንዳለው ሰዎች አድኑን እያሉ በመስኮት እጃቸውን ሲያውለበልቡ ተመልክቻለሁ ብሏል።

እሳቱ ወደ ሌሎች ወለሉ እየተዛመተ የነበረ ቢሆንም ሰዎች በጭንቅ ሆነው ነገር ግን ለመዝለል ፍቃደኛ የነበሩ አይመስለኝም ሲልም ተናግሯል።

የኒው ዮርክ ገዥ ካቲ ሐቹል የትናንቱን አደጋ አሳዛኝ ያሉት ሲሆን ለተጎጂዎች የሚሆን ማካካሻ የገንዘብ ፈንድ እንደሚዘጋጅ ቃል ገብተዋል።

ብሮንክስ ሰፈር ሙስሊሞች በብዛት የሚኖሩበት አካባቢ እንደሆነና ከተጎጂዎች ብዙዎቹም ከጋምቢያ ወደ አሜሪካ የተሰደዱ እንደሆኑ ተዘግቧል።