ከሥራቸው እንደሚለቁ የተነገረው ጄፍሪ ፌልትማን ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፈሪ ፌልትማን ዛሬ ሐሙስ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ለመገናኘት አዲስ አበባ ይገባሉ።
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ማክሰኞ ዕለት ፌልትማን በዚህ ጉዟቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመወያየት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት ለማብቃት ግፊት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ፌልትማን ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የህወሓት ኃይሎችን ከአማራ እና አፋር ክልል ድል አድርጌ አስወጥቻለሁ፤ ህወሓት ደግሞ 'ስልታዊ ማፈግፈግ' አድርጌ ወታደሮቼን ወደ ትግራይ መልሻለሁ ባሉበት ወቅት ነው።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የህወሓት ኃይሎች ከአጎራባች ክልሎች መውጣታቸው እና የፌደራሉ መንግሥት ጦሩን ወደ ትግራይ አለመላኩ፤ ተዋጊ ኃይሎች ለድርድር እንዲቀመጡ እድል ይሰጣል ብለው ነበር።
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን በዋናነት በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በተመለከተ መፍትሔ ለመፈለግ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ መረጋጋት የራቃትን ጎረቤት ሱዳንንም ጉዳይ በቅርቡ ይከታተሉ ነበር።
ተሰናባቹ ፌልትማን
ፌልትማን ዛሬ በኢትዮጵያ የሚጀምሩት ጉዟቸው በልዩ መልዕክተኝነት ለዘጠኝ ወራት ለቆዩበት የመጨረሻ ተልዕኳቸው ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ፌልትማን የትግራዩ ጦርነት መጀመርን ተከትሎ በጆ ባይደን አስተዳደር የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ቀጠናው ይመለሳሉ።
ተልዕኳቸውን ለማሳካት ፌልትማን ከበርካታ የቀጠናው እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት መሪዎች፣ አካባቢያዊ ተቋማት እና ከረድኤት ድርጅት ኃላፊዎች ጋር መክረዋል።
አምባሳደሩ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን በአዲስ አበባ እንዲሁም የህወሓት ተወካዮችን ደግሞ በናይሮቢ ጭምር አግኝተው ማነጋገራቸውን ከሳምንታት በፊት ተናግረው ነበር።
ይሁን እንጂ ፌልትማን እንደ ጥረታቸው በትግራይ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን አስካሁን በጠረጴዛ ዙሪያ ለንግግር እንዲቀመጡ ማድረግ አልተቻላቸውም።
የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ ምዕራባውያኑ ግጭቱ እንዲቆም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲገቱ እና የሰብዓዊ እርዳታ ያለ አንዳች ክልከላ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ሲጠይቁ ሰንብተዋል።

የፎቶው ባለመብት, US Embassy Ankara
በፌልትማን ቦታ የሚተኩት አምባሳደር ሳተርፊልድ
ሮይተርስ የዜና ወኪል አምባሳደር ፌልትማን በቀጣይ ሦስት ሳምንታት ውስጥ ከአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክነት ቦታቸው እንደሚነሱ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ላለፉት 9 ወራት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ያገለገሉት ጄፈሪ ፌልትማን፤ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው እየሰሩ ባሉት ዴቪድ ሳተርፊልድ ይተካሉ።
በቱርክ ከአሜሪካ ኤምባሲ ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ፤ አምባሳደር ሳተርፊልድ በመካከለኛው ምሥራቅ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀ ልምድ እንዳካበቱ ያትታል።
አምባሳደር ሳተርፊልድ በቱርክ፣ ሶሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌባኖስ ኃላፊነቶችን ተቀብለው ሰርተዋል።
አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ማይክ ፖምፔዮ ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።
ፌልትማን በኢትዮጵያ ጉዳይ ምን ብለው ነበር?
ፌልትማን ከዚህ ቀደም ያደረጉትን የመጨረሻውን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ የእርሳቸውን እና የመንግሥታቸውን አቋም በተመለከተ በዝርዝር ተናግረው ነበር።
ፌልትማን ኅዳር አጋማሽ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ የሚያስችል ጅምር ተስፋ መኖሩን፤ ይሁን እንጂ የውይይት ጥረቶች በፍጥነት በሚለዋወጡ ሁኔታዎች ይደናቀፋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸው ነበር።
በእርግጥም እንዳሉት ወደ አፍሪካ ቀንድ የመጨረሻ ጉዟቸውን አድርገው ከተመለሱ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተቃርበው የነበሩት የህወሓት ኃይሎች ወደ ኋላ ተመልሰው፤ መንግሥት በአፋርና በአማራ ክልል ያሉ ሁሉንም ቦታዎች ከአማጺያኑ ማስለቀቁን ገልጿል።
ይህም ድርድር የሚኖር ከሆነና አምባሳደሩ ቀደም ሲል ተስፋ ሰጪ ባሉት የሽምግልና ጥረታቸው ላይ ለውጥን ማስከተሉ እንደማይቀር ይታመናል።
አምባሳደሩ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ገጽ ላይ በወጣው ጽሑፋቸው እአአ 2015 ላይ በ2021 የአፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ ጉዳይ ምን ሊሆን ይችላል ተብዬ ብጠየቅ በቀዳሚነት የማስቀምጠው፤ ሶማሊያን ነበር ይላሉ።
ሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ቀጠናውን የምታረጋጋዋ እና የአሜሪካ ቁልፍ አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ 2021 በዋይት ሐውስ ዋና መወያያ አጀንዳዬ ትሆናለች ብዬ በጭራሻ አልገምትም ነበር ብለዋል።
ፌልትማን እርሳቸው እና የአሜሪካ መንግሥት ላይ ከሚሰነዘሩባቸው ትችቶች መካከል አንዱ 'ለህወሓት ወገንተኛ ናችሁ' የሚለው አንዱ እንደሆነ ከዚህ ቀደም ገልጸዋል።
አምባሳደሩ፤ "የትኛውንም ቡድን አንደግፍም። ለአንዱ ወገንተኛ ናቸው የሚለው አሉባልታ ሐሰት ነው" ሲሉ ጽፈው ነበር።
ፌልትማን ማን ናቸው?
ጄፍሪ ፌልትማን በሹመታቸው ወቅት በተለይ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስላሉ ሁኔታዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አስታውቆ ነበር።
ፌልትማን በድርድርና የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ጥናትን በማካሄድና በአደራዳሪነትም ከፍ ያለ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።
ፌልትማን በፖለቲካዊና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞውንና የአሁኑን ዋና ጸሐፊዎች ባን ኪሙን እና አንቶኒዮ ጉቱሬዝን ያማከሩ ሲሆን፤ ለፀጥታው ምክር ቤት በሠላምና በደኅንነት ጉዳዮች ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።
በተባበሩት መንግሥታት ቆይታቸው ወቅትም በልዩ መልዕክተኝነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ፌልትማን በሊባኖስ፣ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በሃንጋሪና በሄይቲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው ሰርተዋል።












