ጀርመን ያልተከተቡ ዜጎቿ በሱቆች እና መጠጥ ቤቶች መገኘት አይችሉም አለች

ጀርመን የኮቪድ-19 ክትባት ባልወሰዱ ዜጎቿ ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ጀመረች።

አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የሆነው ኦሚክሮን እንደተገኘባት ይፋ ያደረገችው ጀርመን፤ በቅርቡ ከኮቪድ-19 ካላገገሙ በቀር ክትባቱን ያልወሰዱ ሰዎች በሙሉ መሠረታዊ ባልሆኑ መደብሮች፣ መርሃ ግብር በሚካሄድባቸው እና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች መገኘት አይችሉም አለች።

የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንግላ ሜርክል በመላ አገሪቱ የመዝናኛ ስፍራዎች ክፍት የሚሆኑት ክትባቱን ለወሰዱ ወይም ከበሽታው ላገገሙ ሰዎች ብቻ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ያልተከተቡ ሰዎች ከሁለት በላይ ከሆኑ አብረዋቸው ከማይኖሩ ሰዎች ጋር መገናኘት አይችሉም።

"ሁኔታው እጅግ አደገኛ መሆኑን በመረዳታችን ቀድሞ ከተቀመጡት ጥንቃቄዎች በተጨማሪ ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ አስፈልጎናል" ብለዋል ሜርክል።

የሥልጣን ዘመናቸውን እያጠናቀቁ ያሉት ሜርክል በጀርመን በጥቂት ወራት ውስጥ ክትባት መውደስ ግዴታ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሜርክል ከዚህ ቀደም ዜጎች ክትባት መውሰድ ግዴታቸው መሆን የለበትም የሚል አቋም ሲያንጸባርቁ ነበር።

በአሁኑ ሰዓት በአስገዳጅ ሁኔታ ክትባት መውሰድን በተመለከተ ያላቸው አቋም ተቀይሮ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ "የፓርላማ አባል ብሆን ክትባትን አስገዳጅ ለማድረግ ድምጼን እሰጥ ነበር" ብለዋል።

መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል ውሳኔው በበሽታው የመያዝ መጠንን ለመቀነስ እና በጤና ሥርዓት ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና መቀነስ አላማ ማድረጉን ተናግረዋል።

ሐሙስ ዕለት ጀርመን 73 ሺህ አዲስ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን፤ 388 ሰዎች ደግሞ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ሕይወታቸው አልፏል።

ጀርመን ከጠቅላላ ሕዝቧ ለ70 በመቶ የቀረበ ዜጋዋን መከተብ ብትችልም ይህ አሃዝ ከተቀሩት የአውሮፓ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው።