ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አል ቡርሐን እራሳቸውን የሱዳን ጊዜያዊ መሪ አድርገው ሾሙ
በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት በመምራት ወታደሩ ሥልጣን እንዲይዝ ያደረጉት ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሐን አዲስ ምክር ቤት ሲመሠርቱ እራሳቸውን ደግሞ መሪ አድርገው ሰይመዋል።
ሐሙስ ዕለትም ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።
ጄነራል ቡርሐን፤ ምክትላቸው መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችን ከጥቅምት 25ቱ መፈንቅለ መንግሥት በፊት በነበራቸው ሥልጣን እንዲቆዩ አድርገዋል።
14 አባላት ያሉት የሽግግር ምክር ቤት ሲቪል ዜጎችን ቢያካትትም ከመፈንቅለ መንግሥቱ በፊት ሥልጣን ላይ ከነበረው የፖለቲካ ጥምረት አንድም ወኪል አልተካተተም።
ከሥልጣን የተባረሩት የሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ሐምዛ ባሎል አዲሱን የአል ቡርሐን እርምጃ የመፈንቅለ መንግሥቱ ቅጥያ አድርገው ገልጸዋል። ሕዝቡ "አሸንፎ ሽግግሩን ያስቀጥላል" ብለዋል።
ምክር ቤቱ የተቋቋመው መፈንቅለ መንግሥቱን ለመቀልበስ ከአገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ አካላትም ጫናው በጨመረበት ወቅት ነው።
በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ተወካይ ቮልከር ፔርዝስ፤ የጦሩ ዋና አዛዥ ጄነራል አል ቡርሐን የሰጡት የአንድ ወገን የምክር ቤት ሹመት፤ አገሪቱ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመመለስ እንድትቸገር ያደርጋታል ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት መልዕክተኛው የሱዳንን ፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ በአስቸኳይ ድርድር እንዲካሄድ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ጦሩ የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን ሙሉ ነጻነት መመለስን ጨምሮ ሌሎች "የመተማመኛ እርምጃዎችን" እንዲወስድም አሳስበዋል።