የጸጥታው ምክር ቤት በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የጎላ ሚና አይኖረኝም አለ

የፎቶው ባለመብት, FBC
በሱዳንና በግብጽ ጥያቄ መሰረት ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚቀጥለው ሳምንት ይሰበሰባል የተባለው የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የጎላ ሚና እንደማይኖረው ተገለጸ።
በሐምሌ ወር የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሆኑት በተባበሩት መንግሥታት የፈረንሳይ አምባሳደር የሆኑት ኖኮላስ ደ ሪቪዬር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የጸጥታው ምክር ቤት በሚቀጥለው ሳምንት በግድቡ ዙሪያ ወይይት ሊያደርግ ይችላል።
ነገር ግን ምክር ቤቱ ሦስቱን አገራት በመጥራት ስጋታቸውን እንዲገልጹና ከስምምነት ሊያደርሳቸው ወደሚችለው ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታታት ውጪ ሊያደረግ የሚችለው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
"ምክር ቤቱ ከዚያ የበለጠ ሊያደርግ የሚችለው ነገር አለ ብዬ አላስብም" ብለዋል ሰብሳቢው የፈረንሳይ አምባሳደር።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት በሳምንታት ውስጥ ለማከናወን በተቃረበችበት ጊዜ ሱዳንና ግብጽ ከጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በተጨማሪ ጉዳዩን ወደ አረብ ሊግ በመውሰድ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል።
ኢትዮጵያ ወደማጠናቀቁ እየተቃረበችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ድርሻችንን በመጉዳት ለችግር ይዳርገናል የሚሉት ሱዳንና ግብጽ ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነት ሳይፈረም የውሃው ሙሌት እንዳይከናወን እየወተወቱ ነው።
ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመጭ የተነገረለት ግዙፉ ግድብ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር የጎላ ጉዳት በታችኛው ተፋሰሱ አገራት ላይ አያስከትልም በማለት፤ ስምምነት ተደረስም አልተደረሰ በዚህ የክረምት ወር ሁለተኛውን ዙር ሙሌት እንደምታከናውን ኢትዮጵያ አሳውቃለች።
በተደጋጋሚ ያለስምምነት ሲቋረጥ የቆየው የሦስቱ አገራት ድርድር ውጤት ሳያስገኝ በመቅረቱ ሱዳንና ግብጽ ጉዳዩን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲመለከተው ከመጠየቃቸው ባሻገር ሌሎች ምዕራባውያን አገራት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ግን የግድቡ ድርድር ጉዳይ እየተካሄደ ባለበት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር መጠናቀቅ እንዳለበት በመግለጽ ሌሎች አደራዳሪዎች እንዲገቡበት መጠየቅ "የሕብረቱን ጥረት ማንኳሰስ ነው" በማለት ውድቅ አድርጋዋለች።
የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱን አገራት ለማሸማገል ለተራዘመ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በየትኛውም ድርድር ሁሉንም ከሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ አልቻሉም።
ግብጽና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምናገኘውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡን ውሃ ለ65 ሚሊዮን ዜጎቿ የኤሌትሪክ ኃይል ለማቅረብ የምጠቀምበት በመሆኑ ችግር አይፈጥርም በማለት ስጋታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።
ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፤ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በመጪው ከሳምንታት በኋላ እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያስታወቀች ሲሆን፤ ግድቡ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።















