ትግራይ ውስጥ የአየር ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት የተከሰተው ምን ነበር?

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለው የገበያ ሥፍራ በኢትዮጵያ አውሮፕላኖች መምታቱን ተከትሎ እርስ በእርሱ የሚጋጩ መረጃዎች እየተሰራጩ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሆኑን ቢገልጽም በርካታ ምንጮች ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

የተከሰተውን ዝርዝር ለማወቅ የምስክሮችን መረጃ፣ የሳተላይት ምስሎችን እና ይፋዊ መግለጫዎችን የቢቢሲ ፋክት ቼክ ቡድን ተጠቅሟል።

ጥቃቱ እንዴት ነበር የተከሰተ

ማክሰኞ ሰኔ 15/2013 ዓ.ም ከ7፡00 ሰዓት በኋላ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ታዳጊ በአካባቢው ገበያ ውስጥ ካሉ ሱቆች በአንዱ ውስጥ እየተጫወተ ሳለ ነበር ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ የሰማው።

"በፍጥነት ስወጣ ብዙ ሰዎች ተጎድተው መሬት ላይ ወድቀው አየሁ። ከአካባቢው ለማምለጥ ስሮጥ እግሬ ተጎዳ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ፍንዳታው የተከሰተው በቶጎጋ ከተማ የገበያ አካባቢ ሲሆን ቦታው ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 25 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው።

ከቢቢሲ ትግርኛ አገልግሎት ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት ምስክሮች እና ተጎጂዎች ከጥቃቱ በፊት ጊዜውን እና የነበረውን ትዕይንት ገልጸዋል።

በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 07፡37 ላይ የተፈጠረውን ክስተት በመጥቀስ በትግራይ ውስጥ የሚገኝ ተቃዋሚ ቡድን ባለሥልጣን ከሆኑት አንዱ የሆነው ኃይሉ ከበደ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ያሰፈረው ጽሁፍ ሰዓቱን ያመለክታል።

በገላጣ ቦታ ላይ ለሚደረግ ንግድ አገልግሎት የሚውለው ገበያ በሸቀጣሸቀጥ መደብሮች፣ በውበት መጠበቂያ መሸጫዎች፣ በልብስ ስፌት ቤቶች እና በቡና ቤቶች የተከበበ ነው።

የሚሳኤል ጥቃት ሲፈጸም አንዲት ወጣት በገበያው ውስጥ ስተገበያይ ነበር።

እሷ ስትወድቅ እና ሌሎችም በዙሪያዋ መሬት ላይ ሲወድቁ ታስታውሳለች።

ከጥቃቱ የተረፉት ሰዎች መቀለ ወደሚገኘው ሆስፒታል መድረስ የቻሉ ሲሆን ከዚያም ሆነው ታሪካቸውን ተናግረዋል።

አንድ የአካባቢው የአውቶቡስ አሽከርካሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው "ትዕይንቱ እጅግ ዘግናኝ ነበር" ብሏል።

"ቤቶች ፈርሰዋል። ሰዎችም በፍርስራሹ ስር ተቀብረዋል። የተወሰኑ ሰዎችን እና አስከሬኖችን ማውጣት ከባድ ነበር።"

ከተጎዱት መካከል አስራ አምስት ሰዎችን በአውቶቡሱ ወደ መቀለ በሚወስደው መንገድ መጓዙን ቢገልጽም በጦር መኮንኖች እንዲመለስ እንደተነገረው ይናገራል።

ወደ ቶጎጋ በተመለሰበት ወቅት ከተጎጂዎች መካከል አምስቱ ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል።

አንድ የትግራይ የጤና ቢሮ ኃላፊ አምቡላንስ ወደ ቦታው ለመላክ መሞከራቸውን ለቢቢሲ ገልጸው የኢትዮጵያ ጦርን የደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች ከመንገድ ተመልሰዋል ብለዋል።

ከጊዜያዊው አስተዳደር የፍቃድ ደብዳቤ እንዲያመጡም ታዝዘው ነበር።

ደብዳቤውን ይዘው ሲመለሱ ተጨማሪ ደብዳቤ ከክልሉ ፕሬዝዳንት እንዲያመጡ ታዘዙ። ይህ ግን የማይቻል ነበር።

ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞችም እንቅስቃሴያቸውን የሚያደናቅፍ ተመሳሳይ ታሪኮችን ሪፖርት አድርገዋል።

"ፍንዳታው አውዳሚ ነበር"

አቶ ከበደ ጥቃቱን ተከትሎ በገበያው አካባቢ የደርሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ደብዛዛ የሳተላይት ምስሎችን ለጥፈዋል።

የአከባቢው ነዋሪዎች በመጀመሪያ የጄት አውሮፕላን ድምጽ የሰሙ ሲሆን ከጥቂት ሰከንዶች በኋላም ታላቅ ፍንዳታ ሰምተዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አካባቢው ድንጋያማ በመሆኑ ፍንዳታው አውዳሚ ነበር" ብለዋል።

"ደቡባዊው የገበያው ክፍል ቆርቆሮው ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም የሰሜኑ የገበያ ክፍል ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰበት።"

"የጓደኛዬ ሁለት ልጆች ተጎድተዋል። አንዱ ህይወቱ ሲያልፍ ሌላኛዋ ደግሞ እግሯ ተቆርጧል" ይላሉ።

ቶጎጋ እዳጋስሉስ ተብሎም ይጠራል። የማክሰኞ ገበያ እንደማለት ነው። ማክሰኞ ደግሞ የጥቃቱ የደረሰበት ቀን ነው።

አቶ ከበደ ገበያው በዚያ ዕለት በጣም የተጨናነቀ መሆን አለበት ይላሉ። ምክንያቱ ደግሞ ከአካባቢው የእርሻ ወቅት በአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የመጣ የገበያ ቀን በመሆኑ ነው።

"የእርሻ ዘር ለመግዛት የሚመጡ አርሶ አደሮች እንዲሁም ሌሎች ሸቀጦቻቸውን የሚሸጡበት እና የእርሻ ግብዓቶችን የሚገዙበት ቦታ ነው። ይህ መቀለ ዙሪያ ካሉ በጣም ደማቅ ገበያዎች አንዱ ነው።"

የኢትዮጵያ መንግሥት ምን አለ?

ጥቃቱ በተፈጸመበት ማክሰኞ ምሽት ቢቢሲ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ የሆኑትን ኮሎኔል ጌትነት አዳነን አነጋግሯል።

በወቅቱ ገበያው አውሮፕላኖች መምታቱን አስተባብለዋል።

"እኛ በጭራሽ በገበያው ላይ የአየር ጥቃት አልፈጸምንም። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሠራዊቱ ዒላማዎቹን በትክክል የመምታት ብቃት አለው" ብለዋል።

"የአየር ጥቃቶችን አካሂደናል። ነገር ግን በተወሰኑ ዒላማዎች ላይ ብቻ ነበር። በገበያው ላይ ጥቃት ተፈጽሟል የሚባለው ፍጹም የተሳሳተ ነው።"

ባሳለፍነው ሐሙስ ኮሎኔል ጌትነት አዲስ አበባ ለሚገኙ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች እንደገለጹት ጥቃቱ የተፈጸመው የሰማዕታት ቀንን በሚያከብረው የታጠቀው የትግራይ አማጺ ቡድን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የአየር ጥቃቱ የተካሄደው "ገበያው ሊጠናቀቅ በሚችልበት ከ 09፡00 ሰዓት በኋላ ነው" ቢሉም ቢቢሲ ያናገራቸው የዓይን እማኞችና የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ግን ጥቃቱ ገበያው ደምቆ በነበረበት 07፡00 ሰዓት አካባቢ መሆኑን ያመለክታሉ።

ኮሎኔል ጌትነት ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ጦሩ በቶጎጋ ሲቪል ልብስ በለበሱ ታጣቂዎችን መምታቱን አስታውቀው ጥቃቱ በገበያ ቦታ እንዳልተፈጸመ አክለዋል።

የትግራይ ኃይሎች በአካባቢው ነበሩ?

ለዚህምንም የምናውቀው መልስ የለንም።

ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞችም ሆነ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች የክልሉ ተደራሽነት በጣም የተገደበ ነው።

መንግሥት በክልሉ ግጭት እንዳለ ጠቁሞ የትግራይ ኃይሎች በአካባቢው እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አመልክቷል።

ቶጎጋ ወደ መቀሌ በሚወስደው እና በቅርቡ ከባድ ግጭት በተካሄደበት ቦታ መካከል ያለ ስፍራ ላይ ትገኛለች።

ማክሰኞ ዕለት በከተማዋ ገበያ ውስጥ ወይንም በገበያው አካባቢ ተዋጊዎች መገኘታቸውን ማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለም።

በቦታው የነበሩ ሰዎች ታጣቂዎቹ በአካባቢው አለመኖራቸውን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ቢገልጹም፤ በአካባቢው ያሉ ሲቪሎች የአማጺያኑ ታጣቂዎች በስፋራው ነበሩ ብለው ይናገራሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ግልጽ የሆነው ነገር ግን በገበያው አካባቢ በደረሰው ጥቃት በደርዘን ከሚቆጠሩ ጉዳቶች መካከል ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ብዙ ሲቪሎች ይገኙበታል።