የቀድሞው ኮማንዶ የአሁኑ ሚሊየነር አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ናፍታሊ ቤኔት

የእስራኤል ፓርላማ ለ12 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገሪቱን የመሩትን ቤንያሚን ኔታኒያሁን እንዲተኩ ናፍታሊ ቤኔትን መርጧል።

የቀድሞው የማንዶ እና አሁን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ተሰማርተው ሚሊየነር የሆኑት አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ናፍታሊ ቤኔት ኔታኒያሁን በጠባብ ድምጽ በልጠው ነው የአይሁዳዊቷ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት።

ቤኔት ከቤንያሚን ኔታንያሁ ይበልጥ ወደ ቀኝ የሚያዘነብሉ እና የፍልስጤም መንግሥት ፅንሰ ሐሳብን የማይቀበሉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋለ።

የቤኔት ጠቅላይ ሚንስትር የመሆን ምኞት ረዥም ጊዜ የቆየ ነው። ቀኝ ዘመሙ ብሔርተኛ ፓርቲያቸው ያሚና ባለፈው አገር አቀፍ ምርጫ ጥቂት መቀመጫዎችን ብቻ በማግኘቱ ሹመቱን መጠበቃቸው አስገራሚ ነበር።

ፓርቲያቸው ሰባት የፓርላማ መቀመጫዎችን በማግኘት አምስተኛ ሆኖ ነበር ምርጫውን ያጠናቀቀው። በዚህም ከሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ወደ አንዱ ካዘነበሉ መንግሥት የመመስረት ዕድል ስለነበራቸው ቤኔት 'ንጉሥ ሰያሚ' ለመሆን በቅተዋል።

እአአ ከ2009 ጀምሮ በሥልጣን ላይ በነበሩት ኔታንያሁ እና በተቃዋሚው መሪ ያይር ላፒድም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር።

ቤኔት ሰፊ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ቢኖራቸውም ከላፒድ ጎን ለመቆም መርጠዋል።

የ49 ዓመቱ ናፍታሊ ቤኔት ከ2006 እስከ 2008 ድረስ ከኔታንያሁ ጋር መሥራታቸውን ተከትሎ ደጋፊያቸው ተደርገው ይወሰዱ ነበር። በኋላ ግን ተለያዩ።

የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲን ለቀው ወጡ። ቀኝ ዘመሙን 'ጄዊሽ ሆም' ፓርቲን በመቀላቀል እአአ በ2013 በተካሄደው ምርጫ አሸንፈው ፓርላማ ገብተዋል።

እስከ 2019 ድረስ በእያንዳንዱ ጥምር መንግሥት ውስጥ ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል። በዚያው ዓመት ግን ፓርቲያቸው ምንም መቀመጫ ማግኘት አልቻለም ነበር። ከ11 ወራት በኋላ ቤኔት የያሚና ሊቀ መንበር በመሆን ወደ ፓርላማው ተመለሱ።

ከኔታንያሁ የበለጠ "ቀኝ ክንፍ ነኝ" ሲሉ ራሳቸውን የሚገልጹት ናፍታሊ ቤኔት፤ የአይሁድ ብሔረሰብ የአይሁድ ታሪካዊ እና ሐይማኖታዊ የይገባኛል ጥያቄዎች የሚያነሱባቸውን ዌስት ባንክ፣ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም እና የሶሪያን የጎላን ኮረብቶች ባለቤትነት ይደግፋሉ።

ምንም እንኳን እስራኤል በጋዛ ላይ ምንም ዓይነት የይገባኛል ጥያቄ እንደሌላት ቢናገሩም በዌስት ባንክ የአይሁዶችን የሰፈራ መብት ሲደግፉ ቆይተዋል።

በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕገ ወጥ ቢባልም እስራኤል ከ600,000 በላይ አይሁዶች በዌስት ባንክ እና በምሥራቅ ኢየሩሳሌም በሚገኙ ወደ 140 ገደማ ሰፈሮች ማስፈሯ ትክክለኛ ነው ትላለች- እስራኤል።

የሰፈራዎቹ ዕጣ ፈንታ ከእስራኤል እና ከፍልስጤም ያለመግባባት ምክንያት አንዱ ነው። የሰፈራ እንቅስቃሴን ማቆም ይቅርና ጣልቃ መግባቱን ቤኔት አይቀበሉትም።

ሥራውን የሚደግፉት ኔታንያሁን በጉዳዩ ላይ እምነት የሚጣልባቸው አድርገው አይቆጥሯቸውም።

የእንግሊዘኛ ቋንቋን አቀላጥፈው የሚናገሩትና ለመገናኛ ብዙሃን ቅርብ የሆኑት ቤኔት በተደጋጋሚ በውጭ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ተገኝተው የእስራኤልን ውሳኔ ደግፈዋል።

አንድ ጊዜ በአገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያ ክርክር ላይ እስራኤላዊ-አረብ የፓርላማ አባል አይሁዶች በዌስት ባንክ የመኖር መብት የላቸውም ማለታቸውን ተከትሎ "እናንተ ከዛፍ ዛፍ ስትዘሉ እዚህ የአይሁድ መንግሥት ነበረን" ሲሉ ተደምጠዋል።

ቤኔት ከእስራኤል ጎን ለጎን የፍልስጤም መንግሥት መመስረት የሚለውን ሐሳብ አይዋጥላቸውም። ለእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት መፍትሔ እንዲሆን የሁለት-መንግሥት ተብሎ የሚጠራውና በአሜሪካ እና በጆ ባይደን እንዲሁም በብዙ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚቀርበውን መፍትሔ አይቀበሉም።

እአአ በየካቲት 2021 በሰጡት ቃለ መጠይቅ "እኔ ማንኛውም ኃይል እና ቁጥጥር እስካለኝ ድረስ ከእስራኤል ምድር አንድ ሴንቲ ሜትር አሳልፌ አልሰጥም" ብለዋል። ይልቁንም ቤኔት የእስራኤልን የዌስት ባንክ ይዞታ በጉልበት ማጠናከርን ይደግፋሉ።

ቦታዎቹንም በመጽሐፍ ቅዱስ የዕብራይስጥ ስም ጁዲያ እና ሰማርያ በሚለው ስማቸው ይጠሯቸዋል።

ቤኔት የፍልስጤም ታጣቂዎችን ስጋት ለመቋቋም ከባድ አቋም በመውሰድ የሞት ቅጣትን እደግፋለሁ ብለዋል። እአአ በ1961 በኢየሩሳሌም ተፈርዶበት በቀጣዩ ዓመት ከተሰቀለው የናዚ እልቂት መሐንዲሱ አዶልፍ ኢክማን በስተቀር ይህ ቅጣት በእስራኤል በጭራሽ አልተተገበረም።

በ2018 ከጋዛ የሃማስ አስተዳዳሪኦወች ጋር የአስራኤል መንግሠት የካካሄደውን ውዝግብ ያስቆመውን እርቅ አጥብቀው ተቃውመዋል።

ባለፈው ግንቦት ወር ከጋዛ የተተኮሱትን ሚሳኤሎች ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው ምላሽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን በጅምላ አስገድለዋል በሚል ይከሰሳሉ።

የቤኔት የፖለቲካ ከፍታ ቀደም ሲል በወታደራዊ እና በንግድ ውስጥ ያስመዘገቡትን ይከተላል።

በሠራዊቱ አገልግሎት ወቅት በእስራኤል ልዩ ኃይል ሁለት ቅርንጫፎች ውስጥ አገልግለዋል። የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን በማቋቋም እና በመሸጥ ሚሊየነር ለመሆን ችለዋል።

በ2014 ባደረጉት በቃለ መጠይቅ ወቅት ስለ ሀብታቸው ሲናገሩ፤ "ከልክ በላይ አልበላም፣ የግል አውሮፕላን ወይም ጀልባም የለኝም። [ሀብቱ] በቃ የፈለግኩትን ለማድረግ ነጻነት ገዝቶኛል" ብለዋል።