በፈረንሳይ የፌስቡክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የኮቪድ-19 ክትባትን እንዲያጥላሉ ገንዘብ ቀረበላቸው

ፋይዘር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በፈረንሳይ ማንነቱ ያልታወቀ አንድ አካል በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦችን እያደነ የኮቪድ-19 ክትባትን ካጥላላችሁልኝ ከፍተኛ ገንዘብ እሰጣችኋለሁ እያለ በማባበል ላይ ነው፡፡

ደለብ ያለ ገንዘብ እንደቀረበላቸው ያመኑ በርካታ የፌስቡክ፣ የዩትዩብና የኢኒስታግራም ዝነኞች ጉዳዩን አደባባይ አውጥተውታል፡፡

ማንነቱ ያልታወቀው ይህ ገንዘብ ከፋይ አካል/ድርጅት መቀመጫውን በዩኬ እንዳደረገ ቢገመትም ሊደረስበት ግን አልቻለም፡፡

ዝነኞቹን በገንዘብ የሚያማልለው ኢሜይል እየላከ ሲሆን በተለይም ፋይዘር የተባለውን የክትባት ዓይነት ዘዴኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲከፍቱበት ዝነኞችን ያባብላል፡፡

ለምሳሌ በዩትዩብ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት ሊዮ ግራሴት እጅግ የሚያማልል ገንዘብ እንደቀረበለት በትዊተር ሰሌዳው አጋልጧል፡፡

ገንዘብ ያቀረበለት ድርጅት በሊክንድኢን ገጹ ሠራተኞቹ በሩሲያ እንደሚገኙ እንደሚያመላክትም አስረድቷል፡፡

ሊዮ ጨምሮ እንዳጋለጠው ድርጅቱ ክትባቱን ሲያጥላላ በፍጹም ገንዘብ እንደተከፈለው እንዳይናገር እና ቪዲዮም ስፖንሰር እንደተደረገ እንዳይገልጽ በዚህ ድርጅት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡

‹‹የስም ማጥፋት ማስታወቂያ ሲሰራ ቪዲዮውን በራሴ እንደሰራሁት እንድናገር ገፋፍተውኛል›› ብሏል ሊዮ፡፡

ሊዮ ይኸው ድርጅት ፋይዘር የተባለውን ክትባት የሚወስዱ ሰዎች አስትራዜኒካ ከወሰዱት ጋር ሲነጻጸሩ በሦስት እጥፍ ሞታቸው እንደተፋጠነ እንዲናገር ጠይቆታል፡፡

ከሊዮ በተጨማሪ በርካታ የፈረንሳይ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ዝነኞች በተመሳሳይና ለተመሳሳይ እኩይ ተግባር ከፍ ያለ ገንዘብ እንደቀረበላቸው መናገር ጀምረዋል፡፡

በኢናስታግራም 85 ሺህ ተከታዮች ያሉት ሌላ ዝነኛ ለፈረንሳይ ቲቪ እንደተናገረው ለ30 ሰከንድ የስም ማጥፋት ቪዲዮ 2 ሺህ ዩሮ ቀርቦልኛል ብሏል፡፡

የፈረንሳይ የጤና ሚኒስትር ኦሊቪየር ቬራን ይህ ገንዘብ ለዝነኞች የሚረጨው ድርጅት የት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ድርጊቱ ግን አሳፋሪ ነው ብለዋል፡፡

በሁለት ዙር የሚሰጠው ፋይዘር ክትባት ሙሉ ስሙ ፋይዘር እና ባዮንቴክ ሲሆን በፈረንሳይ ለሕዝብ በብዛት እየተሰጠ ያለ የክትባት ዓይነት ነው፡፡

ክትባቱን የፈጠሩት የአሜሪካው ፋይዘርና የጀርመኑ ባዮንቴክ በሽርክና ነው፡፡

ሌላው በሁለት ዙር የሚሰጠው አስትራዜኒካ በፈረንሳይ በ2ኛ ደረጃ እየተሰጠ ሲሆን የሚያመርተው ደግሞ የዩኬና ስዊድሽ ጥምረት የሆነ ፋርማሱቲካል ኩባንያ ነው፡፡

ባለፈው መጋቢት የአውሮጳ ኅብረት አንድ ሪፖርት የሩሲያና የቻይና ሚዲያዎች በምዕራቡ ዓለም እየተሰጡ ያሉ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ኅብረተሰቡ በጥርጣሬ እንዲያያቸው ለማድረግ ውስጥ ውስጡን ይሰራሉ ሲል ከሶ ነበር፡፡

ሞስኮ ይህንን ክስ አጣጥላዋለች፡፡