ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢዜማ የምርጫው መራዘም 'ምክንያታዊ' ነው ሲል ባልደራስ በበኩሉ 'ማብራሪያ እፈልጋለሁ' አለ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የምርጫው መረዘም ምክንያታዊ ነው ሲል ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ( ባልደራስ) በበኩሉ ቦርዱ ምርጫውን በሚያራዝምባቸው ቀናት ውስጥ የሚያከናውናቸውን ተግራት በዝርዝር ማሳወቅ አለበት አለ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከቀናት በፊት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማካሄድ የሚየስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች በወቅቱ ሊጠናቀቁ ሚችሉበት ሁኔታ ስለሌለ ምርጫው በሳምንታት ሊራዘም ይችላል ማለቱ ይታወሳል።
ሰኔ 5 በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ እንዲሁም ከትግራይ በስተቀር በተቀረው የአገሪቱ ክፍል ደግሞ ግንቦት 28 የድምጽ መስጫ ቀን ይሆናል ተብሎ እቅድ ተይዞ ነበር።
ምርጫ ቦርድ ከሎጂስቲክ ሥራዎች መጓተት ጋር በተገናኘ ምክንያት ነው የታቀደው ምርጫ በሁለት ወይም በሦስት ሳምንታት ማራዘም ሊያስፈልግ ይችላል ያለው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ትናንት ምንም እንኳ አስተዳደራቸው በመጀመሪያው ዕቅድ መሠረት ለመቀጠል ፍላጎት ቢኖረውም፤ በምርጫ ቦርድ በኩል ምርጫውን ለአጭር ጊዜ ለማዘግየት ያቀረበው ሐሳብ "ምክንያታዊ በመሆኑ በዚያው ተስማምተናል" ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።፡
የምርጫው መራዘም ምክንያታዊ ነው
የኢዜማ ፓርቲ የሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ፤ የድምጽ መስጫው ቀን እንዲራዘም የቀረበው ሐሳብን "በእኛ አመለካከት ምክንያታዊ ሆኖ ነው ያገኘነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ምርጫውን አጣድፈን ተገቢ የሆነው ዝግጅት ሳይደረግ ተከናውኖ ችግር ውስጥ ከምንገባ ተጨማሪ ጊዜ ተወስዶ እነዚህን ሥራዎች አጠናቆ ምርጫውን ማካሄድ የተሻለ ውጤት አለው" ብለዋል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በሁለት ወይም በሦስት ሳምንት አራዝማለሁ ሲል በሚራዘሙት ሳምንታት ምን እንደሚያከናውን በዝርዝር መታወቅ አለበት ብለዋል።
"ምርጫ ቦርድ ምርጫ አራዝማለሁ ሲል ምን ሊሰራ እንደሆነ በዝርዝር ማሳወቅ አለበት። አሁን ላይ ምን እንደሚሰራ ግልጽ የሆነ ነገር የለም" ሲሉ ገለታው ተናግረዋል።
"ምርጫ ቦርድ ጊዜ እፈልጋለሁ ሲል ለምንድነው የሚፈልገው? የሚል አቋም ነው ያለን" ብለዋል።
ፓርቲያቸው የምርጫው ተሳታፊ እንደመሆኑ ምርጫ ቦርድ ጊዜ ለማራዘም ሲጠይቅ ምርጫ ለምን እንደሚያራዝምና በተጨማሪው ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት በዝርዝር መቅረብ እንዳለበት ገልፈዋል።
"ለምሳሌ የሎጂስቲክ እጥረት በእነዚህ ስፍራ አጋጥሞኛል ካለ፤ የሚሰራውን ሥራ እና የሚያስፈልገውን ጊዜ ግልጽ ካደረገ እንስማማለን" ብለዋል።
አቶ ናትናኤል ምርጫው በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻ እና ፍትሃዊ የሆነ ምርጫ የሚካሄድበት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑና ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ምርጫ ለማካሄድ ተሞክሮ ካለመኖሩ አንጻር ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ፓርቲያቸው ቀድሞ ከግምት ያስገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።
አክለውም "ምርጫው መራዘሙ ያን ያህል በምርጫው ላይ የሚኖረንን ምልከታ የሚቀይር አይደለም" ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
ምርጫው በድጋሚ እንዲራዘም የሚደረግ ከሆነ ግን በሕዝብ ያልመረጠን መንግሥት በስልጣን ላይ ማቆየት ስለሚሆን ምርጫው ከሁለት ወይም ሦስት ሳምንት በኋላ መካሄድ አለበት የሚል አቋም ፓርቲያቸው እንዳለው አቶ ናትናኤል ተናግረዋል።
"ከዚህ በላይ ከተራዘመ በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት በስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያደርግ ነው" ይላሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ መራጮች ይሳተፋሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ይፋ ቢያደርግም ቦርዱ በቅርቡ ይፋ ባደረገው አሃዝ መሠረት እስካሁን ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡት ድምጽ ሰጪዎች ቁጥር 36 ሚሊዮን ተሻግሯል።
የምርጫ ካርድ ከወሰዱት መካከል 16.6 ሚሊዮኑ ሴቶች ሲሆኑ ፤ 19.5 ሚሊዮኑ ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡
እንደ ምርጫ ቦርድ መረጃ ከሆነ ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ከተገመተው በላይ የመራጮች ካርድ ከተወሰደባቸው መካከል ናቸው።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የመራጮች ምዝገባ መከናወኑን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል።