ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የማንቸስተር ተጫዋች ሪያን ጊግስ በሴቶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ተከሰሰ
የዌልስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሪያን ጊግስ ሁለት ሴቶችን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ክስ ተመሰረተበት።
ጊግስ ባለፈው ኅዳር ወር ሳልፎርድ ውስጥ በ30 ዎቹ እና በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሴቶች ላይ ጥቃት በማድረስ ተከሷል።
በመጪው ረቡዕ በማንቸስተር ዩናይትድና በሳልፎርድ ፍርድ ቤቶች እንዲቀርብ ዋስትና አስይዟል።
የ47 ዓመቱ ሪያን ጊግስ በሰጠው መግለጫ በፍርድ ቤት ለቀረበበት ክስ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።
"ለሕግ ሙሉ አክብሮት አለኝ። በተጨማሪም የቀረቡብኝን ውንጀላዎች ከባድነት ተረድቻለሁ" በማለት "ስሜን ለማጽዳት ዝግጁ ነኝ" ሲል ገልጿል።
ዘ ግሬትማንቸስተር ፖሊስ እንደገለጸው የፖሊስ መኮንኖቹ ከወራት በፊት በዎርስሊ የተፈጠረን ረብሻ ተከትሎ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ፖሊስ እንዳመለከተው በ30 ዎቹ ዕድሜ ላይ ያለች አንዲት ሴት በቦታው ለደረሰባት ቀላል የአካል ጉዳት ህክምና አግኝታ ነበር።
ጊግስ እአአ በታኅሣሥ 2017 እና በኅዳር 2020 መካከል ባሉት ጊዜ ውስጥ የማስገደድ ወይም ጫና የማሳደር ባህሪ በማሳየት ተከሷል።
የዌልስ እግር ኳስ ማኅበር የአውሮፓ ዋንጫ ላይ የዌልስን ብሔራዊ ቡድንን የሚመራው ረዳት አስልጣኙ ሮበርት ፔጅ እንደሆነ አረጋግጧል።
"ጉዳዩ በማኅበሩ እና በብሔራዊ ቡድኑ ላይ ስላለው ተፅዕኖ ለመወያየት" የቦርድ ስብሰባ እንደሚኖር ማኅበሩ ገልጿል።
ጊግስ በመግለጫው አክሎም "ለሮበርት ፔጅ፣ ለአሰልጣኞቹ፣ ለተጫዋቾቹ እና ለደጋፊዎች በውድድሩ ስኬታማ እንዲሆኑ ምኞቴን ማስተላል እፈልጋለሁ" ብሏል።
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ የክንፍ መስመር ተጫዋች ጊግስ 24 ዓመት የተጫዋችነት ዘመኑ በሽልማቶች የተሞላ ነበር። እአአ በ2007 የቢቢሲን የዓመቱ ምርጥ የስፖርት ሰው አሸናፊም ሆኗል።
ለዌልስ ብሔራዊ ቡድን በ64 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል። ጥር 2018 ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመ ሲሆን ቡድኑንም ለዩሮ 2020 አብቷል።
ጊግስ በሊግ ሁለት ተወዳዳሪ የሆነው የሳልፎርድ ሲቲ ቡድን ባለቤቶች መካከል አንዱ ነው።