ባይደን በኢራን በሚደገፉ ሚሊሺያዎች ላይ የአየር ድብደባ እንዲፈጸም ፈቀዱ

የአሜሪካ ጦር በሶሪያ የሚገኙና በኢራን በሚደገፉ ሚሊሻዎች ላይ ያነጣጠረ የአየር ድብደባ ማድረጉን ፔንታጎን ገለጸ።

በጥቃቱ "በርካታ በኢራን የሚደገፉ የታጣቂ ቡድኖች በሚጠቀሙበት የድንበር መቆጣጠሪያ ቦታ የሚገኙ በርካታ ተቋማትን ወድመዋል" ብሏል።

በቅርቡ በአሜሪካ እና በአጋሮቿ ላይ በኢራቅ ለተፈፀሙ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ነው ፕሬዝዳንት ባይደን ይህን የአየር ድብደባ እንዲደረግ ያዘዙት።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ኢራቅ ውስጥ አሜሪካ ላይ ባነጣጠረ የሮኬት ጥቃት አንድ ሲቪል ሠራተኛ ተገደሏል።

በዚህ የሮኬት ጥቃት ኢርቢልን ጨምሮ በአሜሪካ የሚመራው ጥምረት በሚጠቀሙበት የጦር ሰፈር የሮኬት ጥቃት ተፈጽሞ አንድ የአሜሪካ ወታደራዊ አባል እና አምስት ሌሎች ሲቪል ሠራተኞች ቆስለዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲን እና የሌሎች ዲፕሎማቲክ መቀመጫ የሆነውን ግሪን ዞንን ጨምሮ በባግዳድ የሚገኙትን የአሜሪካን የጦር ሰፈሮችም በሮኬቶች ተመተዋል።

እንደፔንታጎን ገለጻ ሐሙስ በምስራቅ ሶሪያ በተካሄደው ዘመቻ ኢላማ የተደረጉት ካታይብ ሄዝቦላህ እና ካታይብ ሳይድ አል-ሹሃዳ የተባሉ ሁለት የሚሊሻ ቡድኖችን ነው።

ጥቃቱን "ተመጣጣኝ ወታደራዊ ምላሽ" ያለው ፔንታጎን ከ"ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች" ጎን ለጎን የጥምር ኃይሉን በማማከር የተወሰደ ነው ሲል ገልጿል።

ፔንታጎን በመግለጫ "እርምጃው የማያሻማ መልዕክት ያስተላልፋል" ብሏል።

"ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካ እና የጥምር ኃይሉን አባላት ለመጠበቅ እርምጃ ይወስዳሉ። በተመሳሳይም በምስራቃዊ ሶሪያም ሆነ በኢራቅ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ወደ የሚቀንስ እርምጃ ወስደናል" ሲል አጠናቋል።