ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ አየር መንገድ ቦይንግ 777 አውሮፕላኖችን ከበረራ አገደ
የአሜሪካው ዩናይትድ አየር መንገድ 24 ቦይንግ 777 አውሮፕላኖችን ከበረራ አገደ።
አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹን ከበረራ ያገደው ባሳለፍነው ቅዳሜ ከአውሮፕላኖቹ አንዱ ሞተሩ ላይ አደጋ ካጋጠመው በኋላ ነው።
አውሮፕላኑ 231 መንገደኞችንና አስር የበረራ አስተናጋጆችን አሳፍሮ የነበረ ሲሆን በዴንቨር አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ተገዷል። እስካሁን በአደጋው የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል።
የአውሮፕላኑ ስብርባሪዎችም በአቅራቢያው ባሉ የመኖሪያ ቦታዎች ወዳድቀው ተገኝተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ጃፓን ተመሳሳይ ፕራት እና ዊትኒ 4000 ሞተር የተገጠመላቸውን ቦይንግ 777 አውሮፕላኖችን የሚጠቀሙ ሁሉም አየር መንገዶች አየር ክልሏ እንዳይገቡ ጠይቃለች።
ወደ ሃዋይ ሆኖሉሉ ከተማ ለመብረር የተነሳው ዩናይትድ 328 አውሮፕላን በቀኝ በኩል ባለው ሞተሩ ላይ አደጋ እንደገጠመው የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር ገልጿል።
አደጋውን ተከትሎም አስተዳደሩ የፕራት እና ዊትኒ 4000 ሞተር የተገጠመላቸው ቦይንግ 777 አውሮፕኣኖች ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ አዟል።
"አደጋው ካጋጠመ በኋላ ሁሉንም የደህንነት መረጃዎች ተመልክተናል" ሲሉ የፌደራል አቪየሽን አስተዳዳሪ ስቴቭ ዲክሰን በመግለጫቸው ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ በተገኘው መረጃ መሠረትም፤ ምርመራው በቦይንግ 777 አውሮፕላኖች ላይ ብቻ ለሚገጠመው ለዚህ የሞተር ሞድል የተለየ የሆነው ወደ ሞተሩ ንፋስ ማስገቢያ [ፋን] ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ድምዳሜ ላይ ደርሰናል ብለዋል።
የፌደራል አቪየሽን አስተዳደርም ከሞተር አምራቹ ድርጅት እና ከቦይንግ ተወካዮች ጋር እየተነጋገረ ነው።
የአገሪቷ የመጓጓዣ ደህንነት ቦርድ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ እንደሚያመላክተው አውሮፕላኑ አደጋ ያጋጠመው በቀኝ ሞተሩ ላይ ሲሆን፤ በሌሎች ሁለት ንፋስ ማስገቢያ [ፋን] ተሰነጣጥቀዋል። ሌሎቹም እንዲሁ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይሁን እንጂ የአውሮፕላኑ ዋነኛ አካል ላይ የደረሰው ጉዳት ቀላል መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።
"በኃይል ሲርገፈገፍ ነበር"
ይህ አደጋ ባጋጠመው አውሮፕላን ላይ ተሳፍራው የነበሩት መንገደኞች ለበረራ እንደተነሱ ወዲያውኑ ከፍተኛ ፍንዳታ እንደሰሙ ተናግረዋል።
ከመንገደኞቹ አንዱ የሆኑት ዴቪድ ዴሉሲያ "አውሮፕላኑ በኃይል ሲነቃነቅ ነበር። ከዚያም ከፍ ብሎ መብረር ስላልቻለ ወደ ታች መውረድ ጀመረ" ብለዋል።
አክለውም እርሳቸውና ባለቤታቸው ምንአልባት አደጋ ካጋጠመን በሚል የኪስ ቦርሳቸውን ኪሳቸው ውስጥ እንደከተቱት ተናግረዋል።
የብሩምፊልድ ከተማ ፖሊስ የአውሮፕላኑ የሞተሩ ሽፋን ስባሪ በአንድ መኖሪያ ቤት አትክልት ቦታ ላይ መውደቁን የሚያሳይ ምስል አጋርቷል። ሌሎቹ ስብርባሪዎችም በከተማዋ አንድ የእግር ኳስ ሜዳ ላይ ወድቀው ታይተዋል።
ከአውሮፕላኑ ላይ በወደቀው ስብርባሪ ግን የተጎዳ አለመኖሩ ተገልጿል።
በጃፓን የፕራት እና ዊትኒ 4000 ሞደል ሞተር የተገጠመላቸው ሁሉም 777 አውሮፕላኖች ተጨማሪ ማስታወቂያ እስኪነገር ድረስ አየር ክልሏ መግባት ያቆማሉ። ይህም ለበረራ መነሳትን፣ ማረፍን እና በአገሪቷ የአየር ክልል ላይ መብረርን ያካትታል።
ባለፈው ታህሳስ ወር የጃፓን አየር መንገድ አውሮፕላን በግራ በኩል ያለው ሞተሩ መስራት ባለመቻሉ ወደ ናሃ አየርማረፊያ እንዲመለስ ተገዶ ነበር።
አውሮፕላኑ ባለፈው ቅዳሜ አደጋ ካጋጠመው የዩኒይትድ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር በተመሳሳይ የ26 ዓመት እድሜ ያለው ነው።
በ2018፤ አንድ የዩናይትድ አየር መንገድ አውሮፕላን በሆኖሉሉ ከማረፉ በፊት የቀኝ ሞተሩ ተሰብሮ ነበር። ይህንንም ተከትሎ በተካሄደው ምርመራ የአገሪቷ የመጓጓዣ ደህንነት ቦርድ አደጋው የአውሮፕላኑ ሙሉው የንፋስ ማስገቢያ [ፋን] በመሰንጠቁ ምክንያት ያጋጠመ እንደሆነ አስታውቆ ነበር።