ስንፍናን እንዴት ማስወገድ ይቻላል?

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ዓመት አልፏል። ከዚህ አስጨናቂ ወቅት የምንወጣው መቼ ነው? ለሚለው አሁንም መልስ የለም። በእርግጥ ክትባቶች ተስፋን መፈንጠቃቸው አይካድም።

ወረርሽኙ የበርካቶችን የሕይወት አቅጣጫ ለውጧል። ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ ቋንቋ መማር፣ ቤት ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት ወይም ምግብ ማብሰል መለማመድ የጀመሩ አሉ።

አዳዲስ ነገር የመሞከር ተነሳሽነት ሁሌም አብሮን ይዘልቃል ማለት ግን አይደለም። አንዳንዴ በከባድ ስንፍና ሳቢያ ትንሽ ነገር እንኳ መፈጸም ይሳነናል።

በዚህ ወቅት ራሳችንን ዳግመኛ ማነሳሳት የምንችልባቸውን ጥቂት መንገዶች እንመልከት።

አዲስ ነገር መሞከር

ተነሳሽነት ለራስ የሚጠቅም ተግባር ማከናወን እንዲሁም ለሌሎች መትረፍንም ያካትታል።

ሰውን መርዳት የሚሰጠው ሀሴት ወይም በሚሠሩት ሥራ መደሰት ተነሳሽነትን ይጨምራሉ። እንደ ገንዘብ እና ሽልማት ያሉ ማበረታቻዎችም ያነሳሱናል።

ኮሮናቫይረስ ብዙዎችን ሥራ አልባ አድጓል። ማኅበራዊ ሕይወትንም አላልቷል። እናም በርካቶቻችን ተነሳሽነታችን ጠፍቶ ስንፍና ቢጫጫነን አይገርምም።

የአሜሪካ የሥነ ባለሙያዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ሊን ቡፍካ እንደሚሉት፤ አዕምሯችን መልካም ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ተስፈኛ ለመሆን መሞከር ያስፈልጋል።

ለምሳሌ ስለወደፊቱ ስናስብ የተሻሉ ቀኖች ሊመጡ እንደሚችሉ በማሰብ ተነሳሽነታችንን መጨመር እንችላለን።

በዚህ ምድር ላይ ልንለውጣቸው የምንችላቸው ነገሮች ላይ ማተኮር እና ከአቅማችን በላይ የሆኑትን መረዳትንም ይመክራሉ።

በሕይወታችን የምናገኛቸው ስኬቶች ትንሽም ቢሆኑ ዋጋ መስጠት ያስፈልጋል። አዕምሮ ውስጥ የሚፈጠሩ አሉታዊ ድምጾችን በአወንታዊ ለመቀየርም ይረዳል።

በየጊዜው አዳዲስ ነገር ማድረግን የሚመክሩት ደግሞ ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም አማካሪዋ ኤልዛቤት ግሬስ ሳውደርስ ናት።

"እስኪ ሞክረው የማያውቁትን ምግብ ያብስሉ። በእግርዎ ይንሸራሸሩ። አዲስ ቋንቋ ይማሩ።" ትላለች።

የሚፈልጉትን ማወቅ

በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና መምህር ጋብርኤል ኦቲንገን እንደሚሉት፤ የሁሉም ነገር መጀመሪያ የሚፈልጉትን ማወቅ ነው። ከዚያም የሚፈልጉትን ነገር እንዳያገኙ የሚያግዱ መሰናክሎችን መለየት።

አንድ ነገር ማድረግ ሲፈልጉ፤ ምን ውጤት አገኝበታለሁ? ብሎ በመጠየቅ ተግባርን ከውጤት ጋር ማስተሳሰርን ባለሙያዋ ይመክራሉ።

ለምሳሌ በቀን ለ30 ደቂቃ ለመሮጥ ቢወስኑ ለአካልዎ እንዲሁም ለአዕምሮዎ የሚያስገኘውን ጥቅም አብረው ማሰብ ይችላሉ።

"ስፓርት ከሠራሁ በኋላ ሰውነቴ ይፍታታል፣ ጤናማ እሆናለሁ፣ የተሻለ ቀን አስባለሁ ወዘተ ብለው ያስቡ" ይላሉ የሥነ ልቦና መምህሯ።

በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ መሰናክሎች እንደሚገጥሙ ይጠበቃል። መፍትሔው ግን መሰናክል ፈርቶ መቆም ሳይሆን ችግሩን እንዴት ልለፈው? ወደሚል ስልት መሸጋገር ነው።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ እንደሚሉት፤ "አንድ ነገር ለማድረግ ሲወጥኑ ዝም ብሎ በምኞት ከመዋኘት ምን ችግር ሊገጥመኝ ይችላል ብሎ በብልሀት መጀመር ያዋጣል።"

ከዚያም እቅድ አውጥቶ ወደ ተግባር መግባት።

ወዳጆች ማፍራት

ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ስንፍናን ለማስወገድ በሐሳብ ከእርስዎ ጋር ከሚመሳሰሉ ሰዎች ጋር ትስስር መፍጠር መልካም ነው።

በብሪትሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምረው ስቲቨን ቴይለር "አንድ ነገር የግል ህልም ከሚሆን የጋራ ግብ ሲሆን ተነሳሽነትን ይጨምራል። የእኔ ከሚለው ስሜት ይልቅ የእኛ የሚለው ስሜት ይበልጣል" ይላል።

ከሌሎች ጋር መደጋገፍ መሰናክልን በቀላሉ ለማለፍም ያግዛል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለራሳችን አንዳች ነገር ከማድረግ ይልቅ ለሰዎች ማድረግ ይቀለናል። ስለዚህም አንድን ተግባር ግላዊ ሳይሆን ማኅበራዊ ማድረግ ይመከራል።

በእርግጥ በአንድ ጀንበር ስንፍናን ማስወገድ አይቻልም። ከዓመት ዓመት ተነሳሽነት ያለዎ ሰው ይሆናሉ ማለትም አይደለም።

ሆኖም ግን የሚፈልጉትን ማወቅና አዕምሮዎ አወንታዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ እንደሚያሻ ባለሙያዎች ይመክራሉ።