የሚየንማር ዜጎች ሥራ አቁመው ተቃውሞውን ተቀላቀሉ

በሚየንማር በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት አን ሳን ሱ ቺ እንዲለቀቁ የሚጠይቀው አገራዊ ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው። ሠራተኞችም የሥራ ማቆም አድማ በመምታት ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመዲናዋ ፒ ታው በሚገኙት ያንጎን እና ማንዳሊ አደባባዮች ተቃውሞ እያካሄዱ ነው።

ሚየንማር እንደዚህ ያለ ተቃውሞ ካየች ከአስር ዓመት በላይ ይሆኗታል።

ወታደራዊ ሃይሉ የሚየንማርን መሪ በመፈንቅለ መንግሥት አስወግዶ ለአንድ ዓመት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።

መሪዋ፣ ፕሬዘዳንት ዊን ሚንት እንዲሁም ሌሎችም የገዢው ፓርቲ ኤንኤልዲ አባላት የቁም እስር ላይ ይገኛሉ።

"አንሠራም"

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በኔይ ፒ ታው የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ ነው። በሌሎች ከተሞችም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።

መምህራን፣ ጠበቃዎች፣ የባንክ ሠራተኞችና የመንግሥት ተቀጣሪዎች ከተቃዋሚዎቹ መካከል ይገኙበታል።

በሺዎች የሚቆጠሩ መምህራን ያንጎን ከተባለ ከተማ ሱሌ ፓጎንዳ ወደተባለው ማዕከላዊ ሚየንማር አቅንተዋል።

ሠራተኞች የተቃውሞው አካል እንዲሆኑ ሥራ እንዲያቆሙም በበይነ መረብ ንቅናቄ እየተደረገ ነው።

የ28 ዓመቱ የፋብሪካ ሠራተኛ ሂኒን ታዚን "ዛሬ የሥራ ቀን ነው። እኛ ግን አንሠራም። ደሞዛችን ቢቆረጥም አንሠራም" ሲል ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

በኔይ ፒይ ታው ፓሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን ውሃ እንደተጠቀመና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉም ተዘግቧል።

ተቃዋሚዎች እርስ በእርስ ሲረዳዱና አይናቸውን ሲያሹ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ያሳያል። በየጎዳናው መፈክር ይዘው ድምጻቸውን የሚያሰሙ ተቃዋሚዎችም ታይተዋል።

የሚየንማሩ ኤንኤልዲ ፓርቲ ብሔራዊ ምርጫ አሸንፏል መባሉን ተከትሎ መከላከለያው መፈንቅለ መንግሥት አካሂዷል።

ወታደራዊ ሀይሉ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ተቃዋሚዎችን ደግፏል። ሆኖም ግን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ምርጫው ስለመጭበርበሩ ምንም ማስረጃ የለም ብሏል።

መከላከያው የገንዘብ፣ የጤና፣ የአገር ውስጥ እና የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮችን አንስቶ ሌሎች ባለሥልጣኖች ሾሟል።

ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም የመሳሰሉትን ወታደራዊ ሀይሉ አግዷል።

ከቅዳሜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ተቃውሞ እየተካሄደ ይገኛል። ሚየንማር ውስጥ እንዲህ ያለ ተቃውሞ የተካሄደው እአአ በ2007 ነበር።

በያኔው የሻፍሮን አብዮት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወታደራዊ አገዛዙን ለመቃወም አደባባይ ወጥተው ነበር።