በብሪታኒያ ፌስቡክ የዜና አምድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በብሪታኒያ ፌስቡክ የዜና አምድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ኩባንያው በብሪታኒያ 'ፌስቡክ ኒውስ' የሚል አምድ ከፍቷል። ይህ አግልግሎት በስልኮች በሚጫኑ የፌስቡክ መተግበሪያዎች እንደ አንድ አማራጭ ዜናና ተያያዥ መጣጥፎችን ለማንበብ የሚያስችል ነው።
ፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ የዜናና ሌሎች ጠቃሚ አምዶችን በይዘቱ በይፋ ሳያካትት ቆይቶ ነበር።
አሁን ግን ተጠቃሚዎች ፌስቡክ ሲጠቀሙ ዋና ዋና የዜና አውታሮችን አብረው መቃረም ያስችላቸዋል።
ፌስቡክ ይህን የዜና አምድ አገልግሎት ሲሰጥ ብሪታኒያ 2ኛዋ አገር ናት። ከዚህ ቀደም ይህ አገልግሎት በአሜሪካ መጀመሩ መዘገቡ ይታወሳል።
ፌስቡክ ይህን የዜና አገልግሎት ለመስጠት ከቻናል4፣ ስካይኒውስ እና ዘ ጋርዲያን ጋዜጦች ጋር ልዩ ስምምነት አድርጓል።
ተጠቃሚዎች እነዚህን ይዘቶች ባነበቡ ቁጥር ፌስቡክ ለዜና አውታሮቹ/ጋዜጦቹ ተገቢውን ክፍያ ይፈጽማል።
ጉግል ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ስምምነት በአውስትራሊያ መፈጸም አለብህ መባሉን ተከትሎ አገልግሎቴን ሙሉ በሙሉ በዚያ አገር አቋርጣለሁ ብሎ ሲዝት እንደነበር አይዘነጋም።
አውስትራሊያ እነዚህ የኦንላይን መተግበርያዎች ዜናና ዜና ነክ ይዘትን ለሚያመርቱ ሚዲያዎች ተገቢውን ክፍያ መፈጸም አለባቸው በሚል ጫና እያሳደረችባቸው ይገኛል።
የጉግል አውስትራሊያን ለቅቄ ከናካቴው እወጣለው የሚለው ማስፈራሪያ የመጣውም ይህን ተከትሎ ነው።
የፈረንሳይ ዜና አውታሮች በተመሳሳይ ከጉግል ጋር በዚሁ ጉዳይ በመነጋገር ላይ ናቸው።
ፌስቡክ አሁን በብሪታኒያ የጀመረው የዜና አገልግሎት ይህንን በዜና አምራቾችና በዲጂታል መተግበሪያዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማርገብ የተወሰደ የተናጥል እርምጃ ነው ተብሏል።
ፌስቡክና ጉግልን የመሰሉ መተግበሪያዎች በገቢ ደረጃ ከፍተኛ ትርፍ የሚያጋብሱ ሆነው ሳለ በገቢ ማጣት የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ላሉ የዜና አውታሮች የሚከፍሉት ሽራፊ ሳንቲም አለመኖሩ ፍትሐዊ አይደለም በሚል ሲተች ቆይቷል።
አሁን በብሪታኒያ አዲስ የተጀመረው የፌስቡክ የዜና አምድ ትናንት ከሰዓት ነው በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው።
አገልግሎቱን ማግኘት የሚቻለው የፌስቡክ መተግበሪያን ከከፈቱ በኋላ 'ሞር አፕሽን' የሚለው ውስጥ ገብቶ የዜና አገልግሎት ሰጪ ቴሌቪዥኖችናና ጋዜጦችን ዝርዝር በማየት ነው።
ፌስቡክ የግለሰቦችን እለታዊ ፍላጎትና የልማድ አዝማሚያ በአልጎሪዝሙ አማካኝነት እያጠና ለግለሰቡ ተስማሚ ዜናዎች ሲመጡ ያንን የማቅረብ አሰራርን ይከተላል።
ዜና አውታሮቹ በፌስቡክ መካተታቸው ሁለት ጥቅም ያስገኝላቸዋል ተብሏል።
አንዱ ከፌስቡክ በቀጥታ መደጎማቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እያወቋቸው እንዲመጡና በሂደትም ደንበኛ እንዲሆኑ ሊያበረታታቸው ይችላል፤ አዲስ ገበያም ይፈጥርላቸዋል ተብሏል።
ይህ ፌስቡክ የወሰደው እርምጃ ግብአተ መሬቱ እየተፈጸመ ነው ለሚባለው የፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት እንደ ትንሳኤ እየታየ ነው።












