በአዲስ አበባ ከ21 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘው ተገኙ

በአዲስ አበባ 21,695 የጋራ መኖርያ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘው መገኘታቸውን ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ባለቤት አልባ ህንፃዎች እንዲሁም ኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶች ዙሪያ የተደረገ የማጣራት ውጤት ላይ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም 1,338 ሄክታር መሬት በሕገ-ወጥ የተወረረ መሆኑን፣ 21,695 የጋራ መኖርያ ቤቶች በተለያየ በሕገ-ወጥ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆኑን፣ 322 ግንባታቸው ያለቀና ያላለቀ ህንፃዎች ባለቤት አልባ ሆነው መገኘታቸውን፣ 14,641 መኖርያና ለንግድ የተከራዩ የቀበሌ ቤቶችን ያለ አግባብና በሕገ-ወጥ ይዞታነት የሚገኙ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ ማክሰኞ እለት፣ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ 13 ሚሊየን 389 ሺህ 955 ካሬ ወይም 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት በሕገ-ወጥ መያዙን አስታውቀዋል።
ወይዘሮ አዳነች በዚህ መግለጫቸው ላይ እንዳሉት በአዲስ አበባ በሕገ-ወጥ መንገድ ከተያዙት 21 ሺህ 695 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 15 ሺህ 891 የሚሆኑት የባለቤትነት መረጃ አልቀረበባቸውም።
850 ቤቶች ደግሞ ዝግ ሆነው ሲገኙ 4 ሺህ 530ዎቹ ደግሞ ባዶ ሆነው ተገኝተዋል ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።
እንደ ምክል ከንቲባዋ መግለጫ ከሆነ 424 በሕገ-ወጥ መልኩ በግለሰቦች ተይዘው የሚገኙ ሲሆን በዕጣ ሳይሆን በተለያዩ አግባቦች ወደ ተጠቃሚው ግለሰቦች የተላለፉ ደግሞ 51 ሺህ 64 ቤቶች ሆነው ተገኝተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa City Press Secretary Office
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተባባሰ የመጣ፣ የመንግሥታዊ መዋቅሮች ድጋፍ ያለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላ እንዳለ ባካሄድኩት ጥናት ደርሼበታለሁ ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።
በቤቶች ኮርፖሬሽን ተመዝግቦ የሚገኘው ባለዕጣዎች የስም ዝርዝር እና በመስክ በተገኘው የተጠቃሚዎች የስም ዝርዝር መካከል ልዩነት ያላቸው ቤቶች 132 ሺህ 678 እንደሆኑና 18 ሺህ 423 ቤቶች ደግሞ የቤት ባለቤት ስም የሌላቸው መሆኑን በጥናቱ መለየቱንም አስታውቀዋል።
በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች መረጃቸውን እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም መረጃ ማቅረብ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ በመሆናቸው ቤቶቹ በህገወጥ መንገድ የተያዙ መሆናቸውም በጥናቱ መለየቱን አስታውቀዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
እንደ ምክትል ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ካሉ 121 ወረዳዎች ውስጥ በ88ቱ ወረዳዎች በተፈጸመ የመሬት ወረራ 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት ሲወረር፣ በተደረገው የህንጻ ቆጠራም 322 ህንጻዎች እና ቤቶች ባለቤት አልባ ሆነው ተገኝተዋል።
ከ1997 ጀምሮ በከተማዋ በተለያየ አግባብ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራው ሲፈፀም ነበረ ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፣ በ2010 ሀገራዊ ለውጥ ከመምጣቱ በፊት ሰፋ ባለ መልኩ የመሬት ወረራው የነበረና ከለውጡ በኋላም አጠቃላይ አመራሩ ህገወጥነትን በተገቢው ባለመከላከሉ ችግሩ እንዲደራረብ አድርጎታል ነው ያሉት።
ባለቤት አልባ ቤቶችና ህንፃዎች በተመለከተም ባለቤት አልባ በሚል የተለዩት ቤቶችና ህንፃዎች በድምሩ 322 ሲሆኑ፣ የቦታ ስፋታቸው ደግሞ 229 ሺህ 556 ካሬ መሆኑ መለየቱ ተገልጿል።
እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ መግለጫ ከሆነ፣ ከየወረዳ ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤቶች በተገኘ መረጃ መሰረት አጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚተዳደሩ 150 ሺህ 737 የቀበሌ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶች አሉ።
በዚህ ጥናት ተደራሽ መሆን የተቻለው 138 ሺህ 652 የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን መሆኑም ተገለጿል።
በከተማዋ 10 ሺህ 565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባት፣ እና በሌሎች ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘዋል ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።
በጥናቱ ተደራሽ ከተደረጉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 7 ሺህ 723 ቤቶች ውል በሌላቸው ሰዎች ተይዘዋል።
2ሺህ 207 የቀበሌ ቤቶች ደግሞ ወደግል የዞሩ ሲሆን፣ 265 በሶስተኛ ወገን የተያዙ፣ 164 ኮንደምንየም በደረሳቸው/የራሳቸው ቤት ባላቸው ሰዎች የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው ነው፡፡
137 ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ የቀበሌ ቤቶች በሽያጭ ወደ ግል የተላለፉ፤ 1 ሺህ 243 ታሽገው/ተዘግተው የተቀመጡ፣ 5 ሺህ 43 የፈረሱ፤ 180 አድራሻቸው የማይታዎቁ/የጠፉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ ተረጋግጧል።
የቀበሌ ንግድ ቤቶችን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ በአጠቃላይ የንግድ ቤቶች ብዛታቸው 25 ሺህ 96 ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ የንግድ ቤቶች ብዛት 4 ሺህ 76 ናቸው።
በከተማዋ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ባህሪያት ጋር በተያያዘ በህገወጥ መንገድ ባዶ የሆነ የመንግስትን መሬት በወረራ በመያዝ የተፈፀመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ይህ ድርጊት በግለሰብ ደረጃና በሀይማኖት ተቋማትም ጭምር የተፈፀመ መሆኑ ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።















