ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመድ በትግራይ ክልል የሚፈፀም ወሲባዊ ጥቃት እንዳሳሰበው ገለጸ
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በግጭት ወቅት የሚከሰት ወሲባዊ ጥቃት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ቡድን በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለው ወሲባዊ ጥቃት እንዲገታ አሳሰበ።
የቡድኑ ልዩ ተወካይ ፕራምሊያ ፓተን ሁሉም አካላት ወሲባዊ ጥቃት እንዲገታ እንዲሁም ውጥረት እንዲረግብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ትላንት በወጣው ይህ መግለጫ ልዩ ተወካይዋ "በመቀለ ከተማ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው የመደፈሩ ክስና በአጠቃላይ ከትግራይ ክልል የተሰሙት የወሲባዊ ጥቃት ክሶች እጅግ አሳስበውኛል" ብለዋል።
ጨምረውም "ሰዎች የገዛ ቤተሰባቸውን እንዲደፍሩ እየተገደዱና ይህን ካላደረጉ ጥቃት እንደሚደርስባቸው የሚጠቁሙ በጣም የሚረብሹ ሪፖርቶች ተሰምተዋል" ብለዋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ መንግሥትን ለመጠየቅ ወደ ሚመለከታቸው አካላት ቢሮ ቢደውልም ምላሽ ማግኝት አልቻለም።
የቡድኑ ልዩ ተወካይ ፕራምሊያ ፓተን፤ አንዳንድ ሴቶች መሠረታዊ መገልገያ ለማግኘት ከወታደሮች ጋር ወሲብ ለመፈጸም እንደሚገደዱ ሪፖርት እንደተደረገም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
የሕክምና ተቋሞችን ጠቅሰው ፕራምሊን እንደተናገሩት፤ የእርግዝና መከላከያ እንክብል የሚገዙና በወሲብ የሚተላለፍ በሽታ የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
"ይህም በግጭት ወቅት ወሲባዊ ጥቃት እየደረሰ ስለመሆኑ ማሳያ ነው" ብለዋል።
በስደተኞች ማቆያ የሚኖሩ ሴቶች ስለመደፈራቸው የሚጠቁሙ ሪፓርቶች እየተበራከቱ እንደመጡ በመግለጫው ተመልክቷል።
በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ፣ የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎችን ለመድረስ እንዳልተቻለና በተለይም በስደተኞች ማቆያ ያሉ ሰዎች ጉዳይ አስከፊ እንደሆነ ተናግረዋል።
"ሰብአዊ እንርዳታ ሰጪዎችና ገለልተኛ የመብት ተሟጋቾች ባፋጣኝ ሙሉ ክልሉን እንዲቃኙ መፈቀድ አለበት" ሲሉም አሳስበዋል።
በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉና ስደተኞችም ጭምር ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። በአፋጣኝ የሕክምናና የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲደረግ እንዲሁም ከለላ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
በወታደራዊ ግጭቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በካምፖች ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ አያይዘው በመግለጫቸው ተናግረዋል።
ሽሬ አካባቢ ከ5,000 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ወለል ላይ እንደሚተኙ፣ ምግብና ውሃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። በተጨማሪም ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የተሰደዱ 59,000 ገደማ ኢትዮጵያውን ስለሚገኙበት ሁኔታም ፕራምሊያ ፓተን አንስተዋል።
ለሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውና በቂ ሕክምና መስጫ መሣሪያ አለመኖሩን ጠቅሰው "ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ተገቢው እርዳታ አልደረሰም" ብለዋል።
ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ከኤችአይቪና ሌሎችም በግብረ ስጋ የሚተላለፉ በሽታዎች የሚከላከል ሕክምና፣ የሥነ ልቦና ሕክምናና ሌሎችም መሣሪያዎች ተደራሽ እንዳልሆኑ አስረድተዋል።
"በሰብአዊና ዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርሱ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለሁሉም አካል አሳስባለሁ" ብለዋል።
መንግሥት ንጹሀን ዜጎችን ከወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም ከሌሎች ጉዳቶች እንዲከላከል ሲሉም በመግለጫቸው ተናግረዋል።
መንግሥት ብሔር ሳይለይ ንጹሀን ዜጎችን ከጥቃት እንዲታደግ፣ ወሲባዊ ጥቃቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ እንዲፈቅድና ጥፋተኞችን ተጠያቂ እንዲያደርግ የቡድኑ ልዩ ተወካይ ፕራምሊያ ፓተን አሳስበዋል።