ናይጄሪያ በጥር ወር አጋማሽ የኮሮናቫይረስ ክትባትን እንደምታገኝ ተገለፀ

ናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ ክትባት በጥር ወር አጋማሽ እንደምታገኝ የአገሪቱ የጤና ኤጀንሲ ባለሥልጣን ገለፁ።

ናይጄሪያ በዚህ ዓመት 40 በመቶ ያህል ዜጎቿን ለመከተብ አቅዳ እየተዘጋጀች ሲሆን፤ 30 በመቶ ያህሉን ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት እንደምትከትብ የጤና ኤጀንሲው ኃላፊ ፈይሰል ሲያብ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ዙር ክትባት የተገኘው ከዓለም አቀፉ የክትባት መጋራት ጥምረት፣ ኮቫክስ በኩል ሲሆን ከፋይዘር/ባዮንቴክ 100 ሺህ ክትባቶች ወደ ናይጄሪያ እንደሚላኩ ተገልጿል።

ናይጄሪያ መጀመሪያ ክትባቱን የምትሰጠው ለጤና ባለሙያዎቿ፣ በአደጋ ጊዜ የመጀመሪያ ምላሽ ለሚሰጡ ባለሙያዎች፣ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ግለሰቦች፣ ለአረጋውያን እንዲሁም በተለያየ ሥልጣን እርከን ላይ ለሚገኙ ፖለቲከኞቿ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

እንደ ፈይሰል ሲያብ ገለጻ ከሆነ ናይጄሪይ የአጠቃላይ ሕዝቧን አንድ አምስተኛ ለመከተብ ያቀደች ሲሆን ለዚህም የሚያስፈልጋትን 42 ሚሊዮን ክትባት እንደምታገኝ ተስፋ አድርጋለች።

የዓለም ጤና ድርጅት ኮቫክስ የተሰኘውን የክትባት ጥምረትን የመሰረተው ድሃ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባትን ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ሲሆን ሐብታም አገራት ያለውን ክትባት በሙሉ ጠራርገው ይሸምቱታል የሚል ስጋት በመኖሩ ጭምር ነው።

በተያያዘ ዜና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባለፈው ሳምነት አገራቸው በኮቫክስ በኩል የሚመጣውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት 19.3 ሚሊዮን ዶላር ብትከፍልም፣ የሚደርሳት ግን ከሦስት ወር በኋላ መሆኑን ተናግረው ነበር።

የጤና ሚኒስትሩ ዝዌሊ ማክሄንዚ በበኩላቸው በሚቀጥለው ወር የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማግኘት እንዲቻል ከግል የመድኃኒት አምራቾች ጋር መንግሥታቸው እየተነጋገረ መሆኑን ገልፀዋል።

በደቡብ አፍሪካ በፍጥነት የሚዛመተው ቫይረስ መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ መንግሥት ክትባቱን በአስቸኳይ አምጥቶ ለዜጎቹ እንዲያዳርስ ከፍተኛ ጫና እየተደረገበት ነው።

ደቡብ አፍሪካ 1.1 ሚሊዮን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን በምርመራ አረጋግጣለች። ይህም በአህጉሪቱ ካሉት አገሮች በአጠቃላይ ከፍተኛው ነው።

ናይጄሪያ በበኩሏ እስካሁን ድረስ 100 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ ሲረጋገጥ ከሌላው ጊዜ ሁሉ በበለጠ ሰኞ ዕለት ብቻ 1ሺህ 200 ሰዎች ተይዘው መገኘታቸው ተገልጿል።

ናይጄሪያ 200 ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት በመያዝ ከአፍሪካ ቀዳሚ ነች።