የጉግል ሠራተኞች የመጀመሪያውን የሠራተኛ ማኅበር መሠረቱ

የጉግል እህት ኩባንያ በሆነው አልፋቤት የሚሠሩ ከ 200 በላይ ሠራተኞች ለአሜሪካ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ ባልተለመደ መልኩ የሠራተኛ ማኅበር ለማቋቋም እርምጃዎችን ወስደዋል።

ማኅበሩ በድርጅቱ ውስጥ ያሉ አድሎአዊ አሠራሮችን እና የጥላቻ ንግግርን የመሰሉ ጉዳዮች ስለሚፈቱበት መንገድ ለሠራተኞቹ የበለጠ አቅም ይሰጣቸዋል ብለዋል።

እርምጃው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ እና ሌሎች እርምጃዎችን ተከትሎ የመጣ ነው።

ጉግል "ከሁሉም ሠራተኞቻችን ጋር በቀጥታ መስራቱን እንቀጥላለን" ሲል አስታውቋል።

የሠራተኞች ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ካራ ሲልቨርስተይን በሰጡት መግለጫ "ለሠራተኞቻችን ደጋፊ እና የሚመች የሥራ ቦታ ለመፍጠር ሁሌም ጠንክረን እንሰራለን" ብለዋል።

"በእርግጥ ሠራተኞቻችን የምንደግፋቸውን የሠራተኛ መብቶች አስጠብቀዋል። ሁሌም እንደምናደርገው ግን በቀጥታ ከሠራተኞቻችን ጋር መስራታችንን እንቀጥላለን" ሲሉም አክለዋል፡፡

የአልፋቤት ሠራተኞች ሕብረት እውን ሆነው ጉግል አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና የሥነ ምግባር ተመራማሪ የሆነቸው ትምኒት ገብሩን ማባረሩን ተከትሎ ተቃውሞ ከቀረበበት ከሳምንታት በኋላ ነው።

የአሜሪካ ብሔራዊ የሠራተኞች ግንኙነት ቦርድም በቅርቡ ድርጅቱ ሠራተኞች ማኅበር ለማደራጀት በመሞከራቸው ሠራተኞቹን በሕገወጥ መንገድ የማባረር ውሳኔ አስተላልፏል ብሏል።

ሠራተኞቹም ከመከላከያ የሥራ ክፍሉ እና ከኩባንያው የወሲብ ትንኮሳ ቅሬታዎች አያያዝ ጋር በተያያዘ የድርጅቱን "ፕሮጀክት ማቨንን" ሥራ በመቃወም እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

"ይህ ማኅበር ለዓመታት በጉግል ሠራተኞች በተደራጀ ደፋርነት ላይ የተመሠረተ ነው" ሲሉ የፕሮግራሙ ሥራ አስኪያጅ ኒኪ አንሴልሞ ተደምጠዋል።

"አርእስተቶች ከጠፉም በኋላም ቢሆን አዲሱ ሕብረታችን እንደ አልፋቤት ሠራተኞች የጋራ እሴቶቻችን መከበራቸውን የሚያረጋግጥ ዘላቂ መዋቅርን ያቀርባል" ብለዋል።

ማኅበሩ በሶፍትዌር መሐንዲሶች የተደራጀ ቢሆንም ጊዜያዊ ሠራተኞችን ጨምሮ በኩባንያው የአሜሪካ እና የካናዳ ሥር ላሉ ለሁሉም ተቀጣሪዎች ክፍት ነው ተብሏል።

ማኅበሩን የሚቀላቀሉ አባላት ከሚያገኙት ካሳ አንድ በመቶ ያህሉን ያበረክታሉ።