ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቦይንግ 737 ማክስ በብራዚል ወደ በረራ ሊመለስ ነው
የብራዚሉ ጎል አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ወደ በረራ እንደሚመልስ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሁለት አስከፊ አደጋዎች ደርሰው 346 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ ታግዶ እንደነበር ይታወሳል።
የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ነበር ከበረራ የታገዱት።
ከሦስት ሳምንት በፊት አሜሪካ 737 ማክስ ወደ በረራ እንዲመለስ ውሳኔ አስተላልፋለች።
የብራዚል ግዙፉ አየር መንገድ ጎል እንዳለው፤ 140 የሚሆኑ አውሮፕላን አብራሪዎቹ በአውሮፕላኑ አሜሪካ ውስጥ ሥልጠና ወስደዋል።
ሰባት 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ለ27 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች ማዘጋጀቱን አየር መንገዱ ገልጿል።
እስካሁን 737 ማክስ ወደ በረራ እንዲመለስ የፈቀዱት አሜሪካ እና ብራዚል ናቸው።
አውሮፕላኑ ከበረራ ከታገደ በኋላ ከፍተኛ ማሻሻያ እንደተደረገበት ተነግሯል። ይህም የበረራ መቆጣጠሪያ መተግበሪያውን ማሻሻል እና የበረራ መስተንግዶ ክፍል ሠራተኞችን ሚና መከለስን ያካትታል።
የጎል የኦፕሬሽን ምክትል ፕሬዘዳንት ሴልሶ ፌረር እነዚህን ማሻሻያዎች ተከትሎ በአውሮፕላኑ እንደሚተማመኑ ተናግረዋል።
"ላለፉት 20 ወራት በአቪዬሽን ዘርፍ ትልቁን ክለሳ አድርገናል። ከምንም በላይ የደህንነት ጉዳይ ቅድሚያ ይሰጠዋል" ብለዋል።
የተቋሙ ቃል አቀባይ ለኤኤፍፒ እንዳሉት፤ ተጓዦች በ737 ማክስ መብረር ካልፈለጉ ተጨማሪ ክፍያ ሳይፈጽሙ በረራቸውን ማራዘም ይችላሉ።
"ምንም ገንዘብ ሳይጨምሩ በረራ መቀየር ይችላሉ። የዋጋ ልዩነትም የለም። ትኬቱን ከገዙበት ቀን አንስቶ ባሉት 12 ወራት ከሚፈልጉበት ቦታ ተነስተው ወዳሻቸው ስፍራ መብረር ይችላሉ" ሲሉ ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።
737 ማክስ ወደ በረራ የመመለሱ ዜና ለቦይንግ ትልቅ ብስራት ነው።
ጎል አየር መንገድ አውሮፕላኑን ወደ በረራ ከመመለሱ በተጨማሪ 95 ተጨማሪ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከቦይንግ አዟል።
ከሳምንት በፊት የአየርላንዱ ራየንኤር አየር መንገድ 75 የሚሆኑ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ማዘዙን አስታውቋል።