"ከ50 በላይ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ሰጪ አሰማርተናል" የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር

በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአካባቢው ሰብአዊ እርዳታ እየሰጠ ያለው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በስፍራው ከ50 በላይ የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪ ቡድን ማሰማራቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ እንግዳ ማንደፍሮ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን፤ ከ35 በላይ አምቡላንሶችን አሰማርተዋል።

"የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የትግራይ ቅርንጫፍ እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአማራ ቅርንጫፍ አንድ ላይ የአምቡላንስ አገልግሎት፣ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ አገልግሎትና ሌላም ድጋፍ እያደረጉ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአካባቢው ለሚገኙ ሆስፒታሎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን እየደጎመም መሆኑ ተገልጿል።

"ለተጎዱ ሰዎች የአምቡላንስ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ፤ በምዕራብ ትግራይ አካባቢ ለተፈናቀሉ ሰዎች ምግብ ነክ ያልሆኑ እንደ ብርድ ልብስ እና ፍራሽ ያሉ አስፈላጊ ቁሳቁሶችንም አከፋፍለዋል" ብለዋል አቶ እንግዳ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመሆን ለሆስፒታሎች የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ቁሳቁስ ከአምቡላንስ ጋር እንደሚደርስና ድጋፉ በሽረ፣ መቀለ፣ ወልድያ፣ ዳንሻ፣ ጎንደር እንደተዳረሰ አስረድተዋል።

በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰዎች ላቀረብንላቸው ጥያቄ፤ "እስካሁን እያጓጓዝን ያለነው የተጎዱ ወታደሮችን ነው። ማይካድራ አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው ሰላማዊ ሰዎችን አጓጉዘናል። በሌላ አካባቢ ግን ሰላማዊ ሰዎች አላየንም" ብለው መልስ ሰጥተዋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር በመቀለ አይደር ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች እንዲሁም የአስክሬን ማቆያ የፕላስቲክ ከረጢት እያለቀ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

ሆስፒታሉን የጎበኙ የድርጅቱ ባልደረቦች "80 በመቶው ታካሚዎች በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ሌሎች ሕክምናዎች ቆመው ለድንገተኛ አደጋ ብቻ አገልግሎት እየተሰጠ ነው" ብለዋል።

የማኅበሩ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ማሪያ ሶልዳድ "ቁስል ለመስፋት የሚውል መገልገያ፣ ጸረ ተህዋሲ መድኃኒት፣ የህመም ማስታገሻ እና ሌሎችም መድኃኒቶች በአሳሳቢ ሁኔታ እያለቁ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና በመስጠት ላይ ያሉ በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ መጨናነቅ እንደሚፈጠር የገለጹት አቶ እንግዳ፤ ለሆስፒታሎቹ ድጋፍ እንዲደረግ አሳስበዋል።

ይህ መጨናነቅ ቀደም ያለ ህመም ያለባቸው ሰዎች፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች እና ሌሎችም ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑን አይቀርም።

"ሆስፒታሎቹ ከመደበኛው ውጪ ሥራ ሲኖራቸው ለሌሎች ህመምተኞች እገዛ ለማድረግ ይቸገሩ ይሆናል። ተጨማሪ ፍራሽ እና መድኃኒት የሚጠይቁትም ከመደበኛው ከፍ ያለ ሰው ስለገጠማቸው ነው። እኛም በደረስንባቸው አካባቢዎችም ይህን አስተውለናል። ሆስፒታሎቹ እና ጤና ተቋሞቹ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች ለአካባቢው ማኅረበረሰብ ድጋፍ ለማድረግ መንገዶች ክፍት መደረግ አለባቸው ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች መንገድ እንደሚያመቻች መግለጹ አይዘነጋም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ድጋፍ ለማድረግ እንቅፋት ገጥሟቸው እንደሆነ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ እንግዳ "ሠራተኞቻችን ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቦታው ገብተው እየሠሩ ነው። አሁንም መስራት ቀጥለዋል። የደኅንነት ችግር አይኖርም አይባልም። እንደ ማንኛውም ድርጅት አንዳንድ ቦታዎች የደኅንነት ስጋቶች አሉን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከሦሰት ሳምንታት በላይ በትግራይ ክልል ውስጥ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በህወሓት ኃይሎች መካከል የተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ባለፈው ቅዳሜ የመቀለ ከተማ መያዝን ተከትሎ ዘመቻው ማብቃቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ግጭቱ ከተከሰተበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው ያሉት የግንኙነት መስመሮች አስካሁን በመቋረጣቸው በጦርነቱ የሞቱ ሰዎችና የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ አስተማማኝ መረጃ ማግኘት አዳጋች ሆኗል።

ነገር ግን የተለያዩ የዕርዳታ ተቋማት በሦሰት ሳምንቱ ወታደራዊ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ሳያልፍ እንዳልቀረ ይገምታሉ፤ ቀውሱን በመሸሽም ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሸሻቸው ተነግሯል።

የፌደራል መንግሥቱ መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ በክልሉ ውስጥ መረጋጋትን በመፍጠር ጉዳት የደረሰባቸውን ለመርዳት እየሰራ መሆኑን ከመግለጹ በተጨማሪ ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የገቡ ዜጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።