ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ "የጦር ወንጀል" እንዳይፈጸም ስጋት ገብቶኛል አለ
የተባበሩት መንግሥትታ ድርጅት የ72 ሰዓታት ቀነ ገደቡ ሲጠናቀቅ በመቀለ ሊከሰት የሚችለው ሁኔታ ከወዲሁ አሳስቦኛል አለ። የጦር ወንጀል ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት እንዳለውም ደርጅቱ ከወዲሁ አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ መቀለ ከተማ መቃረቡን ተከትሎ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረት የህወሓት አመራሮች እና የትግራይ ክልል ኃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ ባለፈው እሁድ ምሽት የ72 ሰዓታት የጊዜ ገደብ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የጠቅላይ ሚንስትሩን ጥሪ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል (ደ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ እንደማይቀበሉትና ክልላቸውን የማስተዳደር መብታቸውን ለማስጠበቅ እስከመጨረሻው ለመታገል ብሎም ለመሞት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የህወሓት ከፍተኛ አመራር ጌታቸው ረዳ "እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ ጠመንጅ የያዘም ያልያዘም . . . የሚመክተው ጦርነት ነው" በማለት ሕዝቡ ባለው መሳሪያ እንዲዋጋ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚንስትሩን ጥሪ ተከትሎ በርካታ የትግራይ ኃይሎች እጅ መስጠታቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት አስታውቋል።
ሦስተኛ ሳምንቱን በደፈነው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት በርካቶች ተገድለዋል፣ ከ40ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ቀያቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት አገር ሸሽተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ጦርነቱ ቶሎ ካላበቃ በሚቀጥሉት 6 ወራት ብቻ 200ሺ ዜጎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብሎ ይሰጋል።
የተራድኦ ድርጅቶች የሰብአዊ ቀውሱ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ ምሥራቅ አፍሪካን ሊያተረማምስ የሚችል ችግር ሊፈጥር ይችላል እያሉ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስጋት ገብቶኛል ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የመጨረሻ ይሆናል ባለውና የትግራይ ዋና ከተማ በሆነችው መቀለ በቀጣይ ቀናት ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ወታደራዊ ዘመቻ ነው።
በዋና ከተማ መቀለ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል ተብሎ ይገመታል።
ይህ በአንዲህ እያለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ በማይካድራ ለ600 ሰዎች እልቂት "ሳምሪ" የተባለ ኢ መደበኛ የወጣቶች ቡድንን ተጠያቂ አድርጓል።
ዜጎቹ በግፍ የተጨፈጨፉበት መንገድም "ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ ዘግናኝ የጭፍጨፋ ወንጀል" ነው ሲል ኮሚሽኑ ገልጾታል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ይህ ጥቃት መፈጸሙን የተመለከተ ሪፖርት ቀደም ብሎ ማውጣቱ ይታወሳል። ሆኖም አንድን ቡድን ለይቶ ተጠያቂ አለደረገም።
ህወሓት በበኩሉ ከዚህ ጥቃት ጀርባ የለሁበትም ሲል ክሱን ከዚህ ቀደም አስተባብሏል። ነጻ የሆነ ዓለም አቀፍ ቡድን ክስተቱን እንዲያጣራም ጠይቋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚሸል ባቸሌት በመቀለ ዙርያ ታንኮችና ከባድ መሣሪያዎች ክምችት እየተደረገ መሆኑ ስጋት ፈጥሮብናል ብለዋል።
ኮሚሽነሯ ሚሸል ሁለቱም ወገኖች ለወታደሮቻቸው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ አደጋ እንዳያደርሱ "ግልጽና የማያሻማ" መመርያ እንዲሰጡ አበክረው አሳስበዋል።
"ከሁለቱም ወገኖች የሚሰማው ጠንካራ ዛቻ ነው። የመቀለ ጦርነት ብዙ ንጹሐንን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው። እንዲህ ዓይነት ተቀጣጣይ ንግግሮች የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕጎችን ወደሚጥሱ ሁኔታዎች እንዳያመሩ ስጋት አለኝ" ብለዋል ኮሚሸነሯ።
ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው የኢትዯጵያ መከላከያ ሰራዊት ለዜጎች ጥበቃ እንደሚያደረግላቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ነገር ግን ኮሚሽነር ባቸሌት በትግራይ የግንኙነት መስመሮች ሙሉ በሙሉ በመቋረጣቸው እዚያ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥበቃና ሁኔታ በትክክል ለመገምገም አላስቻለም ብለዋል።
"ሰዎች ትግራዋይ በመሆናቸው ማሰር፣ ከስራ ማፈናቀል፣ ማግለልና ግድያም ጭምር እንዳሉ የሚያሳዩ ሪፖርቶች እየወጡ ነው" ሲል ስጋቱን የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህ እንዲቆም ጠይቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስመልክቶ ስብሰባ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።
በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት ማምራቱ ይታወሳል።
ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻዎች የመንግሥት ኃይሎች የተለያዩ ከተሞችን መያዛቸው የተነገረ ሲሆን በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ አቅራቢያ መድረሳቸውም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ መቀለ የአገሪቱ ሠራዊት ከመንቀሳቀሱ በፊት ሊደርስ ይችላል የተባለ ጉዳትን ለማስቀረት የትግራይ ክልል ኃይሎችን የህወሓት አመራሮች እጃቸውን እንዲሰጡ ነገ ረቡዕ የሚያበቃ የ72 ሰዓታት የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል።