የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ 'ፕራንክ' ተደረጉ

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር የአየር ጸባይ ለውጥ ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግን ድምጽ በማስመሰል በደወሉላቸው ሰዎች 'ፕራንክ' ተደርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመሳሳይ መልኩ ከተሸወዱ ታዋዚ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።

የሰዎችን ድምጽ በማስመሰል እውቅናን ማትረፍ የቻሉት ቭላድሚር ኩዝኔትሶቭ እና አሌክሲ ስቶሪያሮቭ ባሳለፍነው ዓመት ጥር ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሸወዱበትን የስልክ ንግግር የድምጽ ቅጂ ይፋ አድርገዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ግሬት ተንበርግን በመመሰል ስለ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) እና ስለ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸዋል።

''የዓለም መሪ ላይ እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም'' ብሏል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ባወጣው መግለጫ።

አክሎም ''ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የስልክ ጥሪው ሐሰተኛ መሆኑን ሲረዱ ጥሪውን አቋርጠውታል'' በማለት አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ '' ሄሎ ግሬታ፤ እንደምን አለሽ?'' ሲሉ ንግግራቸውን ጀምረዋል።

''እጅግ በጣም ብዙ ኃላፊነቶች እንዳሉብዎት እረዳለሁ፤ ከእንደኔ አይነት ትንሽ ልጅ ጋርም ለማውራት ጊዜ ላይኖርዎት እንደማችልም ይገባኛል። በመላው ዓለም እሆነ ያለው በጣም አሳስቦኛል'' ይላል ግሬታን የሚያስመስለው ግለሰብ።

የስልክ ጥሪው ተደረገው የዩክሬኑ 'ፒኤስ752' አውሮፕላን ከኢራን ዋና ከተማ ቴሄራን ከተነሳ በኋላ ተመትቶ ወድቆ በነበረበት ወቅት ጊዜ ነው። በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ከነበሩት 57 ካናዳ ዜጎች ሲሆኑ፤ ወቅቱ በኢራን እና አሜሪካ መካከልም የነበረው ውጥረት እጅግ የተከራረበት ጊዜ ነበር።

በስልክ ንግግሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ በርካታ የስልክ ጥሪዎችን እየደረሳቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

በመቀጠልም ግሬታን በመምሰል የደወለው ግለሰብ ''የዓለም መሪዎች አዋቂ ሰዎች ቢሆኑም ተግባራቸው ግን እንደ ህጻናት ነው'' ይላል።

''ኔቶን ተዉት፤ መሳሪያዎቻችሁን ጣሏቸው፤ አበባዎችን በእጃችሁ ያዙ፤ በተፈጥሮ ተደስታችሁ ፈገግ በሉ'' ይላል ይሄው ግለሰብ።

በአስተያየቱ ግራ የተጋቡ የሚመስሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለነገሮች ያላትን አስተያየት በማድነቅ በስሜት የተናገረችውን ነገር አድንቀዋል።

ቭላድሚር ኩዝኔትሶቭ እና አሌክሲ ስቶሪያሮቭ ከዚህ ቀደም በቅርቡ ታዋቂው አቀንቃኝ ኤልተን ጆን፣ የእንግሊዙ ልኡል ፕሪንስ እና አዲሷ ተመራጭ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ ላይ ተመሳሳይ ነገር አድርገዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ደግሞ የአርሜኒያን ጠቅላይ ሚኒስትር በመመሰል ቦሪስ ጆንሰን ጋር ስልክ ደውለው ነበር።

አንዳንዶች ጥንዶቹ ከሩሲያ የደህንነት ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በተገዳዳሚ የሚገልጹ ሲሆን እነሱ ግን ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው በማለት ተከራክረዋል።