ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤለን መስክ የማይክሮሶፍቱን ቢል ጌትስን በልጦ የዓለማችን 2ኛው ቢሊየነር ሆነ
የቴክኖሎጂ ፈጣሪው ኤለን መስክ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓለማችን 2ኛው ቢሊየነር ሆነ።
መስክ የማይክሮሶፍቱን ቢል ጌትስን በልጦ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የተቀመጠው።
የኤለን መስክ ሀብት በአጭር ጊዜ የተምዘገዘገው ቴስላ የተባለው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያው በስቶክ ገበያ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ነው።
ይህ ድንገተኛ የሀብት ጭማሪ የኤለን መስክን የሀብት መጠን ከ7 ቢሊዮን ወደ 128 ቢሊዮን አድርሶታል።
የቢሊየነሮችን ዝርዝር የሚያስቀምጠው ብሉምበርግ እንደሚለው ከሆነ በዚህ ሰዓት ኤለን መስክን የሚበልጠው የዓለማችን ቁንጮ ሀብታም የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ ብቻ ነው።
ቴስላ የአሌክትሪክ አምራች በአሜሪካ የስቶክ ገበያ ትልልቆቹን 500 ኩባንያዎች ደረጃ በሚያስቀምጠው ኤስ ኤንድ ፒ (S&P 500) ዝርዝር እንደሚገባ ባስታወቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው የሀብት ግስጋሴው በአስደንጋጭ መልኩ ሽቅብ የወጣው።
የዚህን ዜና መውጣት ተከትሎ በርካታ ሰዎች የቴስላ መኪናን ድርሻ ለመግዛት ሽሚያ እንዲፈጠር አድርጓል። የቴስላ ኩባንያ ጠቅላላ ግምትም ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር አድርሶታል። ይህን ተከትሎ ምንም እንኳ የኤለን መስክ ድርሻ በቴስላ ኩባንያ ውስጥ አነስተኛ ቢሆንም የሰውየው ሀብት ጣሪያ እንዲነካ ምክንያት ሆኗል።
ቴስላ ኩባንያው በዓለም ላይ ከፍተኛ ዋጋ ከሚሰጠው መኪና አምራች ኩባንያ ዋንኛው ነው። ሆኖም ከቶዮታ፣ ቮልስ ዋገን እና ጄኔራል ሞተርስ ጋር ሲነጻጸር የሚያመርታቸው መኪናዎች ብዛት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ማክሰኞ ዕለት መስክ ጀርመን በነበረ ጊዜ የአውሮጳ የመኪና ገበያ ውስጥ መኪና በገፍ የማምረት ሥራ ውስጥ መግባት እንዴት አዋጭ እንደሆነ ሲያስረዳ ነበር።
አሜሪካ ብዙ ሰዎች ትልልቅ መኪና መንዳት ነው ምርጫቸው፤ እዚህ አውሮጳ ግን ትንንሽ ናቸው መኪናዎች፥ ቴስላ በርከት ያለ መኪና በማምረት የዋጋ ተፎካካሪ መሆን የሚችል ይመስለኛል ብሏል መስክ።
ቴስላ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ለተከታታይ ዓመታት ኪሳራን ሲያስመዘግብ ቆይቶ ከዚያ በኃላ ግን ላለፉት ለ5 ተከታታይ ሩብ ዓመታት ትርፋማ እየሆነ ቆይቷል። የትርፍ እድገቱንየኮቪድ ወረርሽኝም አልበገረውም።
መቀመጫውን ካሊፎርኒያ ያደረገው ቴስላ በኤስ ኤንደ ኤስ የስቶክ ማርኬት ግማሽ ትሪሊዮን የሀብት ግምት ዋጋ ይዞ በመግባት የመጀመርያው ነው።
ቢልጌትስ በዓለም የቢሊየኖች ተርታ ለዘመናት ይዞት የቆየውን መሪነት የተነጠቀው በፈረንጆች 2017 ሲሆን አዲሱ ቢሊየነር ደግሞ የአማዞኑ ቤዞስ ነበር።
የቢል ጌትስ ሀብት 127.7 ቢሊየን ዶላር ነው፤ ሆኖም ገንዘቡን በብዛት ለበጎ አድራጎት ስለሚሰጥ እንጂ ከዚህ በላይ የሀብት ግምት ይኖረው ነበር ይላል ብሉምበርግ።
የጄፍ ቤዞስ ሀብት አሁን ላይ 182 ቢሊየን ደርሶለታል። ቤዞስም እንደ መስክ ሁሉ በዚህ ዓመት ገቢው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮለታል። ይህም ወረርሽኙ የበይነ መረብ ግዢ እንዲፋፋም እድል በመፍጠሩ ነው።
ኤለን መስክ ባለፈው ሳምንት የኮቪድ ተህዋሲ ሳይዘኝ አልቀረም ብሎ በትዊተር ሰሌዳው ጽፎ ነበር። መጠነኛ ምልክቶችን ሲያሳይ ነበር።
ኤሎን መስክ በፈጠራት የጠፈር ታክሲ "ስፔስ ኤክስ" 4 የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ የተሳፈሩት በቅርብ ሳምንት ነበር።
ኤሎን መስስ ተወልዶ ያደገው በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ ሲሆን በ17 ዓመቱ ወደ ካናዳ ካቀና በኃላ ለትምህርት በልውውጥ የስኮላርሺፕ ፕሮግራም ወደ አሜሪካ ፔኒሲልቬኒያ ዩኒቨርስቲ ገባ።
በዚያው አጋጣሚ ነው አሜሪካ የቀረው።
አሁን ነዋሪነቱ በአሜሪካ ሎሳአንጀለስ ካሊፎርኒያ ውስጥ ነው። 49 ዓመቱ ሲሆን የ7 ልጆች አባትም ነው።