ትግራይ [ምልከታ] ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ችግር ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው?

ኢትዮጵያ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እያመራች ይመስላል።

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተከፈተው ጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። አገሪቱን ሊከፋፍላት እንደሚችልም ተሰግቷል።

ጦርነቱ የመሣሪያ ብቻ አይደለም። የቃላትም ጭምር እንጂ። ሁለቱም ወገኖች ዜጎችን ከጎናቸው ለማሰለፍና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳመንም እየሞከሩ ነው።

የፌደራል መንግሥትና ህወሓት አንዳቸው ሌላውን ግጭቱን በማጫር ይወነጅላሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የመከላከያ አባላት በጭካኔ ተገድለዋል ይላሉ። የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ደግሞ መከላከያ ሠራዊቱ ከኤርትራ ኃይል ጋር ሆኖ ጥቃት እንደሰነዘረ ይናገራሉ።

መረጃዎቹ በገለልተኛ ወገን እስከሚጣሩ ድረስ አሁን ላይ ማስረጃ የሌላቸው ክሶች ናቸው።

'የጨለማ ዓመታት'

ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን ታሪክ የሚመለከቱት በተለያየ መነጽር ነው።

አብዮቱን ተከትሎ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን ሲወገዱ ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ተተካ። ይህ ወቅት በቀይ ሽብር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የተገደሉበት ነው።

በመላው አገሪቱ ይንቀሳቀሱ ከነበሩ አማጽያን ጋር ረዥም ጊዜ የወሰደ የእርስ በእርስ ጦርነትም ተካሄዷል።

ለትግራይ ተወላጆች እነዚህ ዓመታት ጨለማ ነበሩ። በተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ይካሄድ ስለነበር ሰዎች በሌሊት ለመንቀሳቀስ ተገደው ነበረ።

ከሁሉም የከፋው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ1988ቱ የሀውዜን የአየር ድብደባ ነው። ወደ 2500 ሰዎች ተገድለዋል። የአየር ድብደባውን ተከትሎ ከተማዋ በጭስና አቧራ ሳቢያ በቀን በጨለማ ተውጣ ነበር።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሚመራው የኢሕአዴግ ጥምረት ደርግን አሸንፎ ሥልጣን ከያዘ በኋላ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ "ቀዳሚ ግባችን ኢትዮጵያውያን በቀን ሦስቴ እንዲበሉ ማስቻል ነው" ማለታቸው ይታወሳል።

በ27ቱ ዓመታት የኢሕአዴግ ዘመን የህጻናት ሞት መቀነሱ ይገለጻል። ቀድሞ ከአምስት ልጆች አንድ ይሞት የነበረ ሲሆን፤ ቁጥሩ ከ20 ህጻናት ወደ አንድ ህልፈት ቀንሷል።

ረሀብ ጠፍቷል። መጠነ ሰፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ተወግዷል።

ሆኖም ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ብርሃን አላየችም።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እና ደጋፊዎቻቸው ይህን ወቅት "27 የጨለማ ዓመታት" ይሉታል።

ወጣቱ ትውልድ ድምጹ እንደታፈነ እና ከፖለቲካው እንደታገደ ይሰማዋል።

የትግራይ ተወላጆች ፖለቲካውን፣ ምጣኔ ሀብቱን እና ወታደራዊ ኃይሉን ተቆጣጥረው ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉት የሚከራከሩ አሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሥልጣን የመጡት በዋነኛነት ኦሮሚያ ውስጥ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ተቃውሞ አማካይነት ነው።

ሥልጣን ከያዙ በኋላ የፖለቲካ ምህዳሩን በአንጻራዊነት አሰፉ። ኢሕአዴግን አክስመውም የብልፅግና ፓርቲን መሠረቱ።

እርምጃዎቻቸው እውቅና አተረፉላቸው። ተቺዎቻቸው ግን "ማፍረስ መገንባት አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኤርትራ ጋር እርቀ ሰላም በማውረዳቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት አግኝተዋል። የኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለዓመታት የኢትዮጵያን ወታደራዊ ኃይልና አገሪቷንም የማፍረስ አቋም ቢያንጸባርቁም፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የቅርብ ወዳጃቸው አድርገዋቸዋል።

የፕሮቴስታንት ሐይማኖት ተከታዩ ጠቅላይ ሚንስትር በፈጣሪ የተመረጡ መሪ እንደሆኑ የሚጠቁም ንግግር ሲያደርጉ ይደመጣል።

የሦስተኛ ዲግሪ መመረቂያቸውን ጨምሮ አብዛኞቹ ጽሁፎቻቸው ራስ አገዝ የንግድ ትምህርት ቤት ማስተማሪያ ይመስላሉ።

በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳላቸው አያጠያይቅም።

እሳቸውም ይሁን ፓርቲያቸው በብሔራዊ ምርጫ ቀርበው ምን ያህል ድጋፍ እንዳላቸው ግን ገና አልተፈተሹም።

የሕገ መንግሥቱ ጉዳይ

በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል የነበረው መካረር ጫፍ የደረሰው በትግራይ የተናጠል ክልላዊ ምርጫ ሲካሄድ ነው።

ምርጫው ሕገ ወጥ ነው ሲል የፈደራል መንግሥቱ ውድቅ አድጓል።

በኮቪድ-19 ምክንያት ብሔራዊ ምርጫ ሲራዘም፤ ትግራይ ክልል ለብቻው ምርጫ ካካሄደ በኋላ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዳደር የሥልጣን ጊዜው ስላለፈበት ሕገ ወጥ እንደሆነ ሲገልጽ ነበር።

ሁለቱም አካላት ለመከራከሪያቸው የሚያጣቅሱት ሕገ መንግሥቱን ነው።

ሕገ መንግሥቱ የሰጠው የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ተግባራዊ የማድረግ ጥያቄ ከሚነሳባቸው ክልሎች መካከል ትግራይ እና ኦሮሚያን መጥቀስ ይቻላል።

በእርግጥ ህወሓት ጥያቄውን በግልጽ ባያቀርብም አሁን ላይ ያለው ጦርነት ወደ መገንጠል ሊያመራ ይችላል።

ህወሓት ለ27 ዓመታት የፖለቲካ ምህዳሩን መቆጣጠሩ በኦሮሞና ሌሎችም ብሔሮች ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱ አይዘነጋም።

'አዲሱ ተቃውሞ'

ባለፉት ጥቂት ወራት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ያመጣቸው የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ ላይ ፊታቸውን አዙረዋል።

በተለይም ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ በተነሳው ተቃውሞ ከ150 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ታዋቂ ፖለቲከኞቹ አቶ አጀዋር መሐመድና አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ ወደ 10 የሚደርሱ ሰዎች ታስረዋል።

አቶ ጀዋር በሽብር ሲከሰሱ፤ አቶ ልደቱ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር ተከሰዋል።

በሌላ በኩል ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተገንጥሎ እንደወጣ የሚነገርለት ኦነግ-ሸኔ በቅርቡ በወለጋ ከ50 በላይ የአማራ ተወላጆችን ገድሏል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለግድያው በዘወርዋራ አገላለጽ "አገሪቱን መምራት ወይም ማበላሸት" የሚፈልጉ ያሏቸውን "የኢትዮጵያ ጠላቶች" የሚሏቸውን ህወሓቶችን ተጠያቂ አድርገዋል።

የፌደራል ሥርዓቱ ተገርስሶ አሃዳዊ አስተዳደር እንዲፈጠር የሚሹ የአማራ የፖለቲካ ልሂቃን ለጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፍ አላቸው።

በእርግጥ ብሔርን መሠረት ያደረገ የፌደራሊዝም ሥርዓት በተለያየ ምክንያት ይተቻል። ሆኖም የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለ ፈቃዳቸው ሊመሩ እንደማይችሉ በግልጽ አሳይተዋል።

ከጦርነት ቀጠናው የወጣ ሪፖረት ንጹሃን የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን ይጠቁማል።

ከአዲስ አበባና ከሌሎችም ከተሞች የተገኙ መረጃዎች በትግራይ ተወላጆች ላይ የጅምላ እገዳ እንደተጣለባቸው እያመለከቱ ነው።

በትግራይ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ከመቋረጡ ባሻገር ማንኛውም መጓጓዣ ወደ ክልሉ ስለማይገባ ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስም አልተቻለም።

ህወሓት ትግራይ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ የነበሩ የኤርትራ ወታደሮችን መማረኩን አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ትግራይ ከፌደራል መንግሥቱ በተመደበ መዋቅር እንድትመራ ይሻሉ።

የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ አካላት ይህ ሊሆን እንደማይችል ያምናሉ።

በትግራዩ ጦርነት እጃቸው እንዳለበት የሚነገረው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ እስካሁን ምንም አላሉም።

14 ቀኑን የያዘው ጦርነት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መጥቷል። በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉም ይገመታል።

ይህን ጽሑፍ የተጻፈው በአሜሪካው ተፍት ዩኒቨርስቲ፣ በፍሌቸር የሕግና የዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ውስጥ ሚገኘው የወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሆነው በአሌክስ ደ ዋል ነው።