ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ፕሬዘዳንት የሚመረጠው እንዴት ነው?
በአሜሪካ የምርጫ ሥርዓት አብላጫ ድምጽ ያገኘ ፕሬዝደንት ሆኖ ይመረጣል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ከ100 ሚሊዮን ድምጽ ሰጪዎች 60 ሚሊዮን ያገኘ እጩ ፕሬዝደንት ሆኖ የማይመረጥበት አጋጣሚ ይኖራል።
ለምሳሌ እአአ 2016 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ፤ ሂላሪ ክሊንተን ከትራምፕ በበለጠ በርካታ ድምጽ አግኝተው ነበር። ይህ ግን የአሜሪካ ፕሬዝደንት አላደረጋቸውም።
ለዚህ ምክንያቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የሚመረጠው ቀጥታ በመራጮች ሳይሆን በኤሌክቶራል ኮሌጅ ስለሆነ ነው።
አሜሪካውያን ወደ ፕሬዝደንታዊ የምርጫ ጣቢያዎች ሲያቀኑ ድምጻቸውን የሚሰጡት ኤሌክቶራል ኮሌጅን ለሚጠቀልሉት ፖለቲከኞች ስብስብ ነው።
"ኮሌጅ" የሚለው ቃል የሰዎች ስብስብን የሚያመላክት ነው።
እነዚህ ሰዎች መራጮች ናቸው። ሥራቸውም ፕሬዝደንት እና ምክትል ፕሬዝደንቶችን መምረጥ ነው።
የእነዚህ መራጮች ቁጥር አጠቃላይ 538 ነው።
ግዛቶች እንደ ሕዝብ ቁጥር ብዛታቸው ኤሌክቶራል ኮሌጅ አላቸው።
በርካታ ነዋሪ ያላት ካሊፎርኒያ ግዛት 55 መራጮች (ኢሌክተርስ) አሏት። ይህም ትልቁ ቁጥር ነው።
እያንዳንዱ መራጭ አንድ ኤሌክቶራል ቮት (ድምጽ) ይይዛል። አንድ እጩ ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ፤ ካሉት 538 ኤሌክቶራል ኮሌጅ 270 እና ከዚያ በላይ ያስፈልገዋል።
ግዛቶች የኤሌክቶራል ኮሌጅ አጠቃላይ ቁጥራቸውን በግዛቱ ብዙ ድምጽ ላገኘ አሸናፊ ይሰጣሉ።
ለምሳሌ በቴክሳስ ግዛት 38 ኤሌክቶራል ኮሌጅ አሉ። በዚህ ግዛት ሪፐብሊካኖች 50.1 እንዲሁም ዴሞክራቶች 49.9 ደምጽ ቢያገኙ፤ ሪፐብሊካኖች 38 ኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ጠቅልለው ይወስዳሉ ማለት ነው።
ኔብራስካ ግዛት ግን እጩዎች ባገኙት ድምጽ መሠረት ኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ቁጥርን ታከፋፍላለች።
ይህን ግን በምርጫው አጠቃላይ ውጤት ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አያመጣም።
ሁለቱም እጩዎች አብላጫ ድምጽ ባያገኙ ምን ይፈጠራል?
ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝደንት በመሆን ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ለመቀጠል እንዲሁም ጆ ባይደን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን 270 እና ከዚያ በላይ የሆነ ኤሌክቶራል ድምጽ ያስፈልጋቸዋል።
ሁለቱም እጩዎች 270 ኤሌክቶራል ድምጽ ባያገኙስ?
የአሜሪካ የሕዘብ ተወካዮች ምርክ ቤት ፕሬዝደንቱ ማን ይሁን? በሚለው ላይ ድምጻቸውን ይሰጣሉ።
ይህ የመሆን እድሉ በጣም ጠባብ ነው። በአሜሪካ የምርጫ ታሪክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ፕሬዝደንቱን የመረጠው እአአ 1824 ላይ ነበር።