አሜሪካ፡ በትናንቱ ምሽት ክርክር ትራምፕ እና ባይደን ምን ተባባሉ?

ትራምፕ እና ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን በመጨረሻው የፊት ለፊት ክርክራቸው በኮቪድ-19፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና በዘር ጉዳዮች ላይ ብዙ ተመላልሰዋል።

የትናንት ምሽቱ ክርክር ከመጀመሪያው ዙር የተሻለ እርጋታ የታየበት ነው ተብሏል። እንደዛም ሆኖ ሁለቱ ፖለቲከኞች ግላዊ ጉዳዮችን እያነሱ ሲተቻቹ ነበር።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ጆ ባይደን አሁንም በአሜሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥብቅ ክልከላዎች መጣል አለባቸው ሲሉ ፕሬዝደንት ትራምፕ በበኩላቸው አሜሪካን ክፍት ማድረግ አለብን ሲሉ ተከራክረዋል።

ትራምፕ "ይህ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ያለው ትልቅ አገር ነው" ያሉ ሲሆን "ሰዎች ሥራቸውን እያጡ ነው። ድብርት አለ። ሰዎች ራሳቸውን እያጠፉ ነው" ብለዋል።

ባይደን ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለሞቱት ከ220ሺህ በላይ አሜሪካውያንን ትራምፕን ተጠያቂ አድርገዋል።

"ለዚሁ ሁሉ ሰው ሞት ተጠያቂ የሆነው ሰው ፕሬዝደንት ሆኖ መቆየት የለበትም" ብለዋል።

ዘር ጉዳይ ላይ

ትራምፕ "እዚህ ክፍል ውስጥ ካለን ሰዎች መካከል ዝቅተኛ ዘረኛ ያልሆንኩት እኔ ነኝ" ሲሉ ተደምጠዋል። ትራምፕ እአአ 1994 ላይ የወጣውን የወንጀል መመሪያ በማስታወስ ጆ ባይደን ይህ መመሪያ ሲወጣ ተሳትፎ አድርገዋል ብለዋል። ጥቁር አሜሪካውያን ይህ መመሪያ የጥቁሮችን መብት ይጋፋል ሲሉ ይተቻሉ።

ባይደን በበኩላቸው በአሜሪካ የቅርብ ዘመን ታሪክ ውስጥ ከተመለከትናቸው ዘረኛ ፕሬዝደንቶች መካከል አንዱ ትራምፕ ነው ብለዋል። ባይደን ዘረን መሠረት አደርገው በሚነሱ አለመግባባቶች ላይ ትራምፕ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ወይም በሚወስዷቸው እርምጃዎች ነገሮችን እንደሚያባብሱ ተናግረዋል።

ትራምፕ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ከልጃቸው ሃንተር የንግድ ሥራ ተጠቃሚ ሆኖዋል ሲሉ ጆ ባይደን በበኩላቸው ትራምፕ የሚጠበቅባቸውን ግብር አይከፍሉም ብለዋል።

ስደተኞችን በተመለከተ

ትራምፕ አስተዳደራቸው በደቡብ አሜሪካ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ሰዎች ከልጆቻቸው እንዲነጠሉ ስላደረገው ፖሊሲያቸው ተጠይቀው ነበር።

ትራምፕ በኦባማ ዘመን ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ልጆችም ታስረው ነበር ብለዋል።

የቀድሞ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው የትራምፕ አስተዳደር ወላጆች እና ልጆችን መለየቱ ጭካኔ ነው ካሉ በኋላ ወላጆችን እና ልጆችን መለየት "የወንጀል ተግባር ነው" ሲሉ ትራምፕን ድርጊት ኮንነዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ

ሁለቱ አጩዎች አሁንም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ተመላልሰዋል።

ትራምፕ ጆ ባይደንን "የነዳጅ ኢንደስትሪውን ሙሉ በሙሉ ትዘጋዋለህ?" ሲሉ ጠይቀዋል ባይደን በበኩላቸው "አዎ ከነዳጅ ኢንደስትሪው መላቀቅ አለብን። ምክንያቱም የነዳጅ ኢንደስትሪው ከፍተኛ ብክለት ያስከትላል ብለዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ከነዳጅ ኢንደሰትሪው እንውጣ ቢባለ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሰው ከሥራ ውጪ ይሆናል ብለዋል።

ሌሎች የተነሱ ጉዳዮች

ባይደን በአሜሪካ አንድ ሰራተኛ በሰዓት የሚከፈለው መጠን ከ15 ዶላር ያላነሰ እንዲሆን አደርጋለሁ ብለዋል።

ወረቀት የሌላቸው 11 ሚሊዮን ሰዎች የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ በሩን እከፍትላቸዋሁ ብለዋል ጆ ባይደን።

የአፍ እና አፍንጫ ማድረግን ግዴታ አደርጋለሁ ሲሉም ጆ ባይደን ተናግረዋል።

ፕሬዝደንታዊ ክርክሩን የመራችው ጋዜጠኛ ክሪስተን ዎከር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንታዊ ክርክሩን የመራችው ጋዜጠኛ ክሪስተን ዎከር

ማን አሸነፈ?

በትናንት ምሽት ክርክር ማን ተሽሎ ተገኘ ለሚለው ቁርጥ ያለ ምላሽ የሚሰጥ የተገኘ አይመስልም። እንደ ሲኤንኤን ከሆነ በክርክሩ ላይ ትራምፕ ለ41 ደቂቃዎች የተናገሩ ሲሆን ባይደን በበሉላቸው 38 ደቂቃዎች ያክል ተናግረዋል።

በመጨረሻው ፕሬዝደንታዊ ክርክር ላይ ትራምፕ ያሳዩት እርጋት እና የሰነዘሯቸው መከራከሪያ ሃሳቦችን በርካቶችን አስደንቋል።

የክርክሩ አሸናፊ፡ አከራካሪዋ!

ፕሬዝደንታዊ ክርክሩን ለመራችው ለኤንቢሲ ጋዜጠኛዋ አድናቆት እየቀረበላት ይገኛል። የ44 ዓመቷ ክሪስተን ዎከር አስፈላጊ ሲሆን እጩ ፕሬዝዳንቶቹን ታቋርጥ ነበር።

ክርክሩ ከተጀመረበት ቅጽበት እስከ መጠናቀቂያው ድርስ ክርክሩን መቆጣጠር ችላ ነበር ተብሏል።

12 ቀናት በቀሩት ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ጆ ባይደን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ቅድመ ምርጫ ግምቶች ይጠቁማሉ። እስካሁን ከ46 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

የምርጫ ቅድመ ግምቶች ግን ትክክለኛው የምርጫውን ውጤታ ላያሳዩ ይችላሉ። ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ የቅድመ ምርጫ ውጤቶች ሂላሪ ክሊንተን እንደሚያሸንፉ የሚጠቁሙ ነበሩ።