እርቀ ሰላም ኮሚሽን የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥታት ለማስታረቅ ምን እየሰራ ነው?

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል እና ምክትል ሊቀመንበር የትነበርሽ ንጉሴ

እርቀ ሰላም ኮሚሽን የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥታት ለውይይት ፈቃደኛ ከሆኑ ለማስታረቅ ዝግጁ መሆኑን አሰስታወቀ።

የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩ 21 ግጭቶችን እያጠና መሆኑን ትናንት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጿል።

የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር የትነበርሽ ንጉሴ "ግጭቶችን የመለየት ሥራ ሰርተናል፤ ከእነዚህ ውስጥም በናሙና መልክ በመምረጥ እንዴት መፍታት እንችላለን በሚለው የግጭቶችን መንስዔና ምንነት የማጣራት ሥራ እየሰራን ነው" ብለዋል።

እነዚህ ለዕርቅና ሰላም ፈታኝ ናቸው የተባሉ 21 ግጭቶች በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ የተፈጠሩ መሆናቸው ተነግሯል።

ከእነዚህ ግጭቶች መካከል የተወሰኑት አሁንም ተመልሶ በሚፈጠር ግጭት ለሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆናቸውን የተናገሩት የትነበርሽ ንጉሴ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከተውጣጡ ሽማግሌዎች ጋር ምክክር እንደሚደረግበትም ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልል ጉዳይ

የእርቅና ሰላም ሥራ በሕዝቦች መካከል የሚሰራ መሆኑን የተናገሩት የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል ከዚህ ቀደም የአገር ሽማግሌ ሆነው ሁለቱን መንግሥታት ለማሸማገል በተሳተፉበት ወቅት ያጋጠማቸውን እንዲህ ተናግረዋል "ወደ ክልሎች ሄደን ስናወያያቸው፣ የክልሉ አመራር እኛ ለውይይት ዝግጁ ነን ይሉናል። ለውይይት መድረክ አዘጋጅተናል ስንላቸው ደግሞ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን የማስቀመጥ ሁኔታ አለ" በማለት መልሰዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን አዋጅ በመጥቀስ "የእኛ ትልቁ ኃላፊነት ያለፉትን አለመግባባትና ጉዳቶች ላይ በማተኮር፣ በእነዚህ አለመግባባቶች የተጎዱ ስሜቶችን በመጠገን ስለነገ ሃሳብ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው" ሲሉ የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር የትነበርሽ ንጉሴ ተናግረዋል።

"በፌደራል መንግሥትና በክልል ችግር ሲፈጠር የመፍታት ኃላፊነት የእርቅና ሰላም ኮሚሽን አይደለም" በማለት በፌደራል እና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው አለመግባባትን የመፍታት ኃላፊነት ለኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጡት ሥልጣኖች መካከል አለመሆኑን በመጥቀስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል።

"እንደ ገለልተኛ ኮሚሽን ማድረግ የምንችለው ተረጋግተው አብረው እንዲያወሩ መጠየቅ ነው" በማለት ውይይት እንዲያደርጉ ገለልተኛ አካል የሚያስፈልግ ከሆነ፣ ኮሚሽኑ ዝግጁ መሆኑን የኮሚሽነሩ ምክትል ሊቀመንበር የትነበርሽ ንጉሴ ይናገራሉ።

ሁለቱ አካላት ለውይይት ፈቃደኛ ከሆኑ ለማስታረቅ ዝግጁ መሆናቸውንም ጨምረው አስታውቀዋል።

ሌሎች ጉዳዮች

በአገሪቱ ውስጥ እርቅና ሰላም አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳዩ ነገሮች ቢኖሩም፣ የሰላም አለመኖር ስራቸው ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የተናገሩት የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር የትነበርሽ ንጉሴ፣ መንግሥት የሕዝቡን የእለት ተዕለት ሰላም መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ሥልጣን ላይ ያለውን ጨምሮ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት ምክትል ሊቀመንበሯ፣ ከወጣቶች ጋር እየሰሩ መቆየታቸውንና በሚመጡት ወራትም የኢትዮጵያ አስታራቂ ወጣቶች ፎረምን ለማቋቋም ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውን ተናግረዋል።

ሴቶች በእርቅ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግም፣ የኢትዮጵያ ሴት በጎ ፈቃደኞች እርቅ መድረክ ለማቋቋም ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኮሚሽኑ ለሥራ እንዲዘጋጅ በቂ ጊዜ በመንግሥትም ሆነ በሌላ አካል አለመሰጠቱን የተናገሩት ኃላፊዎቹ፣ ይህም ደግሞ ሥራቸውን እያስተጓጎለ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትህ፣ አንድነት፣ እና የብሔራዊ መግባባት እንዲሁም እርቅ እንዲወርድ ለመስራት አልሞ በ2011 ዓ.ም ላይ የተቋቋመ መሆኑ ይታወሳል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሰላም