ጣልያን፡ አረንጓዴ ፀጉር ይዞ የተወለደው ቡችላ

ፒስታቺዮ አምስት ወንድምና እህቶች አብረውት ተወልደዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጣልያን ውስጥ አረንጓዴ ቀለም ያለው ቡችላ መወለዱ ተሰማ።

ቡችላው በግብርና ሥራ የሚተዳደረው የክርስትያን ማሎቺ ሲሆን፣ ውሻው ስፔላቺያ ስድስት ቡችሎችን በተገላገለች ጊዜ አንዱ አረንጓዴ ፀጉር ይዞ መወለዱ ተነግሯል።

ይህ ከሌሎች ቡችሎች ለየት ብሎ የተወለደው ቡችላ ፒስታችዮ የሚል ስም ተሰጥቶታል።

የፒስታቺዮ እናት አምስት ወንድምና እህቶች አብረውት ተወልደዋል። በጣሊያንዋ ሳርዲና ከተማ የተወለደው ይህ ቡችላ ወንድምና እህቶቹ በአጠቃላይ ልክ እንደናታቸው ነጭ ፀጉርን ይዘው መወለዳቸው ተረጋግጧል።

የእንስሳት ሕክምና ባለሙያዎች ለፒስታችዎ አረንጓዴ ፀጉር ይዞ መወለድ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንዲህ አይነት አረንጓዴ ፀጉር ይዞ መወለድ እጅጉን ያልተለመደ ነው ያሉት ባለሙያዎቹ ነገር ግን አይፈጠርም ማለት አለመሆኑን ፒስታችዎን ማስረጃ አድርገው አስረድተዋል።

ቡችላው በእናቱ ማሕፀን ውስጥ ሳለ ቢልቨርዲን ከሚባል አረንጓዴ ፒግመንት ጋር ንክኪ ነበረው ማለት ነው ብለዋል።

ፒስታቺዮ አምስት ወንድምና እህቶች አብረውት ተወልደዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፒስታቺዮ አረንጓዴ ፀጉሮች ግን አብረውት አይቆዩም፤ የእናቱን ነጭ ፀጉር ወደመያዝ ከአሁኑ እየሄዱ ነው።

ገበሬው ማሎቺ የፒስታቺዮ ወንድምና እህቶች በሙሉ ውሻ እንፈልጋለን ላሉ ሰዎች ለመስጠት ወስኗል። ነገር ግን ፒስታቺዮን በጎች በመጠበቅ ያግዘኛል እኔው አሳድገዋለሁ ሲል ተናግሯል።

ደግሞም ይላል ገበሬው ማሎቺ፣ አረንጓዴ የመልካም እድል ምልክት ነው። በማለት በቀሪው 2020 መልካም ነገር እንደሚገጥመኝ የሚጠቁም ቢሆንስ ብሏል።