የሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን በአሜሪካ ክስ ተመሠረተባቸው

የሳኡድ አረቢያ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን በአሜሪካ የክስ ፋይል ተከፍቶባቸዋል።

ከሳሾቹ ደግሞ የሟቹ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ እጮኛ ሃቲስ ሴንጊዝ እና ኻሾግጂ ከመገደሉ በፊት የመሠረተው የመብት ተሟጋች ቡድን ነው።

በጥምረት የተከፈተው ክስ ጋዜጠኛ ኻሾግጂ እንዲገደል ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ትእዛዝ ሰጥተዋል ይልላ።

የዋሺንግተን ፖስት አምደኛና የመብት ተሟጋቹ ጀማል ኻሾግጂ ከሁለት ዓመት በፊት ነው በኢስታንቡል የሳኡዲ ቆንስላ ውስጥ ዘግናኝ በሚባል ሁኔታ የተገደለው።

ግድያውን ያዘዙት የሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ናቸው የሚል በርካታ ክሶች ይቀርብባቸዋል። ልዑሉ ግን ከደሙ ንጹሕ ነኝ ይላሉ።

ኻሾግጂ ከጋብቻ ወረቀት ማሳደስ ጋር በተያያዘ በቱርክ ኢስታንቡል በሚገኘው የሳኡዲ ቆንስላ እንደገባ ነበር በዚያው በኖ የቀረው።

ያንኑ ዕለት በፍጥነት ከሳኡዲ በልዩ አውሮፕላን የገባ አንድ ነፍሰ ገዳይ ቡድን እጅግ በረቀቀ ሁኔታ ጀማል ኻሾግጂን ገድሎ ከአገር መውጣቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የቱርክ መንግሥት ደርሶበታል።

ልዑሉ ግን እኔ ግድያውን አላዘዝኩም ሲሉ ተከራክረዋል።

ጋዜጠኛና የዋሺንግተን ፖስት አምደኛ ጀማል ኻሾግጂ የሳኡዲ መንግሥት የመብት ረጋጭነትን ሲተች በይበልጥ ይታወቃል።

ከአገሩ ሳኡዲ ከመሰደዱ በፊትም ንጉሣዊያን ቤተሰቡን ያማክር ነበር።

የሟቹ ጀማል እጮኛ የነበረችው ቱርካዊቷ ሴንጊዝ ክሱን እና የመብት ቡድኑ ክሱን የከፈቱት በዋሺንግተን ዲሲ ነው።

ጀማል ካሾግጂ መስርቶት የነበረው ‹‹ዲሞክራሲ ፎር ዘ አረብ ዎርልድ ናው›› የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት ከመሥራቹ መገደል በኋላ ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እንደገባ ተነግሯል።

ይህ ድርጅትም ከጀማል ኻሾግጂ እጮኛ ጋር በመሆን ልዑሉን ከሳሽ ሆኖ ቀርቧል።

‹‹ጀማል በሕይወት ሳለ በአሜሪካ ሁሉም ነገር ይቻላል ይለኝ ነበር። እምነቴን በአሜሪካ የፍትሕ ሥርዓት ላይ ጥዬ ነው ክሱን የከፈትኩት›› ብላለች፣ እጮኛው።

ጀማል ኻሾግጂ ማን ነበር?

ቀድሞ በሳኡዲ ውስጥ ጋዜጠኛ ነበር። አፍጋኒስታን በሶቪየት ኅብረት ስትወረር፣ የኦሳማ ቢን ላደን አነሳስና ሌሎች ትልልቅ ጉዳዮችን ለተለያዩ ሳኡዲ ዜና ጣቢያዎች በመዘገብ ዝናን አትርፏል።

ከዚያ በኋላም ከንጉሣዊያን ቤተሰቦች ጋር ቅርብ ግንኙነት ነበረው። የመንግሥት አማካሪም ሆኖ ሰርቷል።

አንዳች አለመግባባት በመፈጠሩም በፈረንጆቹ 2017 ከሳኡዲ ተሰዷል።

በአሜሪካ መኖር ከጀመረ በኋላም ለዋሺንግተን ፖስት ወርሃዊ አምደኛ ሆኖ ይሰራ ነበር። ሌሎች ተያያዥ የመብት እንቅስቃሴዎችንም በማድረግ ይታወቃል።

በሚጽፋቸው ጽሑፎቹ የሳኡዲው ልዑልና የንጉሥ ሰልማን ልጅ የሆኑት መሐመድ ቢን ሳልማን ላይ የሰላ ሒስ ያቀርብ ነበር።

ከፍተኛ የመብት ረገጣ ባለባት ሳኡዲ ንጉሡንና ቤተሰቡን መተቸት ለሞት የሚዳርግ ነው።

ጀማል በኦክቶበር 2፣2018 በቱርክ ኢስታንቡል ከእጮኛው ጋር ሳኡዲ ቆንስሌት ሄደ።

እጮኛውን ለማግባት የሚያስችለው ወረቀት ለማግኘት እና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመጨረስ። እጮኛው ከዚህ ቆንሱሌት በር ላይ ጠበቀችው። እሱ ገባ። ከዚያ በኋላ አልተመለሰም።

ሬሳውም ቢሆን እስከአሁን የት እንዳለ አይታወቅም።

ምናልባት የኻሾግጂ ሬሳ በልዩ ኬሚካል ተቃጥሎ እንደ ንፋስ እንዲበን ተደርጓል የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ።