ትራምፕና ባይደን የሚለያዩባቸው 8 ቁልፍ ጉዳዮች

እርግጥ ነው እስከአሁን ከ20 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ድምጽ ሰጥተዋል። ይፋዊ የምርጫ ቀኑ 15 ቀናት ብቻ ነው የቀሩት።

ለመሆኑ ጆ ባይደንና ዶናልድ ትራምፕ የፖሊሲ ልዩነታቸው ምንድነው?

1. ኮሮናቫይረስ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- ትራምፕ የኮሮና ግብረ ኃይል አቋቁመው ተህዋሲውን ሲዋጉ ነበር። አሁን የዚህ ግብረ ኃይል ተግባር ተዘግተው የነበሩ ግዛቶች እንዲከፈቱ ማድረግና ሥራ ሞቅ ሞቅ እንዲል ማበረታታት ነው ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ ክትባት በፍጥነት እንዲዳረስ እየሰራሁ ነው ይላሉ። በቅርቡ ሁላችሁም ክትባት ትወጋላችሁ፣ ኮሮና ታሪክ ይሆናል ሲሉም ቃል ገብተዋል። 10 ቢሊዮን ዶላር ለዚሁ መድበዋል።

ጆ ባይደን፡- የትራምፕ ግብረ ኃይል ሕዝብ አስጨርሷል ብለው ያምናሉ። 250ሺ ሕዝብ የሞተው ትራምፕ በሚከተሉት ልል ፖሊሲ ነው ይላሉ። ከተመረጥኩ በብሔራዊ ደረጃ ተህዋሲውን (ተጠቂዎችን) እግር በእግር የሚከታተል ፕሮግራም ይፋ አደርጋለሁ ይላሉ። በአንድ ግዛት በትንሹ 10 የምርመራ ጣቢያ አዘጋጃለሁ ብለዋል። የኮቪድ ምርመራ ለሁሉም ዜጋ በነጻ አደርሳለሁም ብለዋል። ሌላው በብሔራዊ ደረጃ ጭምብል ግዴታ ያደርጋሉ።

2. አየር ንብረት ጉዳይ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- የአየር ንብረት ለውጥ ብሎ ነገር የለም፤ ቅጥፈት ነው ይላሉ። ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል አቅርቦትን ማስፋፋት ይሻሉ። ነዳጅና ጋዝ ፍለጋ እንዲቀጥል፣ እንዲጧጧፍ ያበረታታሉ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት በሚል የሚወጣ ወጪ እንዲቆም ያደርጋሉ። ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ወጥተዋል።

ጆ ባይደን፡- ነጩ ቤተ መንግሥት እንደገቡ ወዲያውኑ ወደ ፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መልሰው ለመግባት ይሻሉ። አሜሪካ በ2050 ዜሮ የካርበን ልቀት ላይ እንድትደርስ ይሰራሉ። 2 ትሪሊዮን ዶላር በአረንጓዴ ታዳሽ ኃይል ያወጣሉ። የነዳጅና ጋዝ ፍለጋ እንዲቆም ያደርጋሉ።

3ኛ፡- በምጣኔ ሀብት ጉዳይ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- በ10 ወራት 10 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር ቃል ገብተዋል። 1 ሚሊዮን አነስተኛና ጥቃቅን ሥራ እፈጥራለሁ ብለዋል። የግብር እፎይታ ለትልልቅ ኩባንያዎች በመስጠት ሥራ ፈጠራ እንዲፋፋም አደርጋለሁ ይላሉ።

ጆ ባይደን፡- ከሀብታም ኩባንያዎች ግብር በመጫን ሕዝቡን የሚጠቅሙ ልማቶች ላይ አተኩራለሁ ይላሉ። ነገር ግን ግብር የምጭነው ገቢያቸው በዓመት 400 ሚሊዮን ዶላር በሚያገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ ብቻ ነው ብለዋል።

በቀን ዜጎች የሚያገኙት ትንሹ የምንዳ ምጣኔ በሰዓት 15 ዶላር እንዲሆን አደርጋለሁ ብለዋል። አሁን ያለው ትንሹ በሰዓት የሚከፈለው 7.25 ዶላር ነው።

4ኛ፡- በኅብረተሰብ ጤና ጉዳይ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- የኦባማ የጤና መድኅን ጨርሶ ለማጥፋት ይፈልጋሉ። በዚህ ‹አፎርደብል ኬር አክት› በሚባለው አዋጅ መሰረት የፌዴራል መንግሥት የግል የጤና መድኅን ሰጪዎችን ይቆጣጠራል። መድኅን ሰጪዎች ቀደም ብሎ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎችን መድኅን ሲጠይቁ የሕክምና ወጪ አልሸፍንም ማለት አይችሉም። ትራምፕ ግን ይህንን ረብ የለሽ ኦባማ ኬር ቀዳድጄ በሌላ ጥዬ በሌላ እተከዋለሁ እያሉ ይዝታሉ።

የመድኃኒት ዋጋ አሁን ካለበት እንዲወርድ አደርጋለሁ፤ በርካሽ ከሌሎች አገሮች መድኃኒት እንዲገባም እፈቅዳለሁ ብለዋል።

ጆ ባይደን፡- የኦባማ የጤና ሽፋን መድኅንን አስጠብቃለሁ ይላሉ። በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚያገኙትን የጤና ትሩፋቶችን አስፋፋለሁ፤ ለዚህ ትሩፋት የሚያበቃውን ዕድሜም ከ65 ወደ 60 አወርደዋለሁ ብለዋል። ሁሉም አሜሪካዊያን የኅብረተሰብ ጤና መድኅን የመመዝገብ ምርጫ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።

5ኛ፡- የውጭ ፖሊሲ ጉዳይ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- በውጭ አገር ያሉ ወታደሮችን ለእናት አገራቸው አበቃለሁ ይላሉ። የንግድ ታሪፍ በቻይና ላይ እጭንባታለው ብለዋል።

ጆ ባይደን፡- ትራምፕ ያበላሹትን የውጭ ግንኙነት አስተካክላለሁ፤ አሜሪካ ያስቀየመቻቸውን ወዳጆቿን ልብ እጠግናለሁ ብለዋል። ከኢራንና ከቻይና ጋር የሚከተሉት ፖሊሲም ትራምፕ ጋር የሚቀረን ነው።

6ኛ፡-ዘርና ዘረኝነትን በተመለከተ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- በአሜሪካ ፖሊስና ጸጥታ አስከባሪዎች ዘንድ መዋቅራዊ ዘረኝነት የለም ብለው ያምናሉ። ፖሊስ ማንቁርት ማነቁን ባይደግፉም ሕግን ማስከበር አለበት፣ ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ መፈቀድ የለበትም ይላሉ። ከፖሊስ ይልቅ ወንበዴዎች የሚሏቸውን ሰልፈኞች ማውገዝ ይመርጣሉ።

ጆ ባይደን፡ -ዘረኝነት በፖሊስና ጸጥታ አስከባሪዎች ዘንድ መዋቅራዊ ቅርጽ ይዟል ብለው ያምናሉ። ይህንንም ለማጥፋት እሰራለሁ ብለዋል።

7ኛ፡- የጦር መሣሪያን በተመለከተ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- ትራምፕ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት 2ኛው ማሻሻያ ለአሜሪካዊያን የጦር መሣሪያ የመታጠቅ ሙሉ መብትን አጎናጽፏል ብለው የተለጠጠ ትርጓሜ ይሰጡታል።

የጦር መሣሪያ ገዢዎች ላይ የኋላ ታሪክ ጥናት መደረግ አለበት ብለው ነበር፣ በ2019 ዓ.ም የደረሱ ግብታዊ ጥቃቶችን ተከትሎ። ሆኖም እስከዛሬ በዚህ ረገድ ተግባራዊ ያደረጉት አንዳችም ነገር የለም።

ጆ ባይደን፡- በጦር መሣሪያ ረገድ ቁጥጥር ማጥበቅ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ የገዢዎችን የኋላ ታሪክ ማጥናትና መመዝገብ፣ አንድ ዜጋ በወር መግዛት የሚችለው የመሣሪያ ብዛት አንድ ብቻ እንዲሆን ማድረግ፣ ቸልተኛ የመሣሪያ አምራቾችና ሻጮችን ተጠያቂ ማድረግ፣ ለዜጎች መሸጥ የሚችሉ የጦር መሣሪያ ዓይነትም በሕግ እንዲወሰን ማድረግ ይፈልጋሉ።

8ኛ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን በተመለከተ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፡- ሕገ መንግሥቱ በሰጠኝ ሥልጣን በሟቿ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ምትክ ሌላ እጩ የመሰየም መብት አለኝ ብለው ያምናሉ። ይህንንም ተከትሎ ወግ አጥባቂዋን ኤሚ ባሬትን በእጩነት አቅርበዋል።

ሴትየዋ ሥራ በይፋ ሲጀምሩ የመጀመርያ ሥራቸው የሚሆነው በአሜሪካ የጽንስ ማቋረጥ መብት ላይ ድምጽ መስጠት ነው። ከዚህ በፊት በነበራቸው አቋም ትራምፕም ሆኑ ባሬት ጽንስ ማቋረጥ በአሜሪካ ሕገ ወጥ እንዲሆን ይሻሉ።

ጆ ባይደን፡- ይህ በጎደሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ምትክ ሰው መሾም ያለበት ከምርጫ በኋላ ነው፣ የግዛት ዕድሜውን እየጨረሰ ያለ ፕሬዝዳንት በአሜሪካ ሕዝብ ፍላጎት ላይ መወሰን የለበትም ብለው ያምናሉ። ጽንስ የማቋረጥ መብት ሕጋዊ እንዲሆንም ይሻሉ፡፡