ኮሮናቫይረስ፡ በኖርዌይ የአንዲት መርከብ ተሳፋሪዎችና ሠራተኞች በቫይረሱ ተያዙ

በኖርዌይ የመዝናኛ መርከብ ላይ ተሳፍረው የነበሩ ቢያንስ 40 መንገደኞችና ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ኤምኤስ ሮልስ አሙንድሰን በተባለችው መርከብ ላይ ተሳፍረው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች መንገደኞች ደግሞ ለይቶ ማቆያ ገብተው የምርመራ ውጤታቸውን እየተጠባበቁ እንደሆነ የመርከቧ ባለንብረት ተናግረዋል።

ሁርቲግሩትን የተባለ የኖርዌይ ድርጅት ንብረት የሆነችው መርከብ በትሮምሶ ወደብ ያረፈችው ባሳለፍነው አርብ ነበር።

በዚህም ሳቢያ ድርጅቱ ሁሉንም የመዝናኛ መርከቦቹን እንዳይንቀሳቀሱ አግዷል።

የድርጅቱ ኃላፊ ዳንኤል ስካይልዳም "አሁን ትኩረት ያደረግነው ባልደረቦቻችንና እንግዶቻችንን ለመንከባከብ የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነው" ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

አራት የመርከቡ ሠራተኞች የኮሮናቫይረስ ምልክት ታይቶባቸው አርብ ዕለት መርከቧ ወደብ ላይ ካረፈች በኋላ ሆስፒታል የገቡ ሲሆን በኋላ ላይ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ከ158 ሠራተኞች መካከልም ሌሎች 32ቱ በቫይረሱ መያዛቸው የምርመራ ውጤታቸው አመላክቷል።

ይሁን እንጂ 180 የሚሆኑ መንገደኞች ከመርከቧ እንዲወጡ የተፈቀደላቸው ሲሆን በባለሥልጣናት ቁጥጥር እንዲመረመሩ ተደርጓል። ሁሉም መንገደኞች ራሳቸውን እንዲለዩ መደረጉንም የጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ በመርከቧ ጉዞ ላይ ከነበሩ 387 ተሳፋሪዎች መካካልም እስካሁን በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠው አምስት እንደሆኑ ተገልጿል።

የጤና ባለሥልጣን የሆኑት ሊን ቮልድ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት አሁን ከተከሰተው የቫይረስ ሥርጭት ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎች ቫይረሱ ሊገኝባቸው እንደሚችል ገልፀዋል።

መርከቧ በአርክቲክ በሚገኘው ስቫልባርድ ለአንድ ሳምንት የቆየች ሲሆን በኢንግላንድና ስኮትላንድ የሚገኙ ወደቦችን ደግሞ መስከረም ላይ ለመጎብኘት እቅድ ይዛ ነበር ተብሏል።

ይሁን እንጂ ኢንዱስትሪው በወረርሽኙ በመመታቱ ሁሉም የወደፊት ጉዞዎች ስለመኖራቸው የታወቀ ነገር እንደሌለ ተገልጿል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወረርሽኙ በመርከቦች ላይ በመዛመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች በባሕር ላይ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ መቆየታቸው ይታወሳል።