ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በየመን ችግር ላይ መሆናቸው ተገለፀ

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በየመን እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ በችግር ላይ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።

ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ተገልጿል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንዳለው ባለሥልጣናት ቢያንስ 14 ሺህ 500 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን መሰረታዊ የጤና እና የንፁህ ውሃ አገልግሎት በማያገኙበት ሁኔታ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ በከፋ ችግር ላይ እንዲወድቁ አድርገዋቸዋል።

አገሪቷ በወረርሽኙ ሳቢያ ድንበሮቿን በመዝጋቷ ስደተኞቹ ያለ ፈቃዳቸው ወደ አደን ፣ ማሪብ፣ ላህጅ እና ሳኣዳ እንዲሄዱ መገደዳቸውንና በእነዚህ ቦታዎች በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ድርጅቱ አትቷል።

ስደተኞቹ ቫይረሱ እንዳለባቸው በማሰብም መገለልና እና ጥቃት እንደደረሰባቸው ድርጅቱ ገልጿል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በየመን የሚገኙ ስደተኞች የቃል እና አካላዊ ጥቃቶች እየደረሰባቸው፣ የእስር ጊዜያቸው እየጨመረ፣ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲሁም ያለፈቃዳቸው መሰረት ልማት በሌለባቸው አካባቢዎች እንዲሄዱ እየተገደዱ ነው።

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመጓዝ የመንን ያቋርጣሉ። በዚህ ዓመት ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የተጣሉ ገደቦች ችግሩን የከፋ አድርጎታል።

ባለፈው ዓመት ከአፍሪካ ቀንድ አገራት፤ አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ የሆኑ 138 ሺህ ስደተኞች ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመግባት በማለም የመን መግባታቸውን ድርጅቱ አስታውሷል።