የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና ያለፈው ሳምንት ክስተት

የዛሬ ሳምንት ሰኞ ምሽት በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚጠቀሙት ፌስቡክ ላይ ታዋቂው የኦሮምኛ ድማጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ አንዳች ችግር እንደተከሰተ የሚገልጹ መልዕክቶች በስፋት መዘዋወር ሲጀምር፤ አብዛኛው ሰው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንዲህ አይነቱ በታዋቂ ሰዎች ላይ የሚነዛ ሐሰተኛ ወሬ ነው ብሎ ትኩረት አልሰጠውም ነበር።

ነገር ግን ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ ለድምጻዊው ቅርብ የሆኑና የሚታወቁ ሰዎችም ሃጫሉ ጉዳት እንደደረሰበት ከታማኝ ሰው መስማታቸውን ሌሎች ደግሞ ማረጋገጣቸውን መግለጽ ጀመሩ። ወዲያው ተከትሎም የድምጻዊው ህይወት ማለፉን የሚገልጹ መረጃዎች ከፎቶው ጋር ማኅበራዊ ሚዲያውን አጨናነቁት።

ክስተቱ ለእውነት የቀረበ እንደሆነ ሲታወቅ ብዙዎችን ከባድ ድንጋጤና ሐዘን ውስጥ በመክተት ከመደበኛዎቹ መገናኛ ብዙሃንና ከመንግሥት የመጨረሻውን ሐቅ ለመረዳት ከአንዱ ቴሌቪዥን ወይም ሬዲዮ ወደ ሌላው በመቀየር ማመን ከባድ የሆነውን እውነታ ለማረጋገጥ በመሞከር ምሽቱ ተጋመሰ።

በመጨረሻም እኩለ ሌሊት አልፎ ሰባት ሰዓት ከሩብ አካባቢ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ጌቱ አርጋው በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በእርግጥም ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት ተመትቶ ለህልፈት የመዳረጉን መርዶ ተናገሩ።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም ከግድያው ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው፤ ፖሊስ በተፈጸመው የግድያ ወንጀል ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክተው ሕዝቡም እንዲረጋጋ ጠይቀው ነበር።

በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመው ግድያ በተሰማበት ጊዜ ጀምሮ እከሌ ከእከሌ ሳይባል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነበር ያስደነገጠው። ክስተቱ ቀድሞ የተሰማበት የማኅበራዊ ሚዲያው መድረክም ከግድያው ጋር በተያያዙ ጥያቄዎችና በድምጻዊው ምስል እንዲሁም የሐዘን መግለጫ መልዕክቶች ተጥለቀለቀ።

ዜናው ይፋ እንደተደረገ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ድንቅና አንፀባራቂ በማለት የገለጹትን ሃጫሉን "ውድ ህይወት አጥተናል" ሲሉ የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹት ሌሊቱ ከመንጋቱ በፊት ነበረ።

ጨምረውም የግድያውን ሙሉ የፖሊስ የምርመራ ሪፖርት እየተጠበቀ እንደሆነ ጠቁመው "የድርጊቱን መጠን በመረዳት በአገራችን ውስጥ ስለሚደረጉ ነገሮች ትኩረት ሰጥተን የምንከታተልበት ወቅት ላይ እንገኛለን" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ተከትለው በድምጻዊው ግድያ ሐዘናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም ግድያውን የፈጸመው ማንም ይሁን ማን ከሕግ ማምለጥ እንደማይችል ገልጸው "ለዚህ እኩይና አስነዋሪ ሥራም ዋጋቸውን በሕግ ያገኛሉ" ሲሉ ለቤተሰቡና ለሕዝቡ ትዕግስት፣ ብርታትና መጽናናትን ተመኝተዋል።

በሃጫሉን እንደ አንድ አብሮ አደግና እንደ ትግል ጓዳቸው የገለጹት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው "ግድያው ተራ አይደለም ታስቦበት የተፈፀመ ነው፤ በዚህ ምንም ጥርጥር የለኝም" በማለት እንደተራ ነገር የሚታለፍ ክስተት እንዳልሆነ አመልክተዋል።

አክለውም ሕዝቡ ክስተቱን በሰከነ ሁኔታ መገንዘብ ተጠርጣሪዎቹን ለፍርድ ማቅረብና የተጀመረው ለውጥ እንዲሳካ "እጅ ለእጅ ተያይዘን በመረጋጋትና በመናበብ ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እንድንሻገር ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ክልሎችና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድምጻዊው ግድያ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው በሕዝቡ ውስጥ መረጋጋት እንዳይጠፋ ጠይቀው ነበር።

የአስከሬን ሽኝት

የሃጫሉ ሞት ከተነገረ በኋላ በመዲናዋ እና በዙሪያዋ ካሉ አካባቢዎች የሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቹና ወዳጆቹ ሌሊቱን በሙሉ ተጉዘው አስከሬኑ ወዳረፈበት ሆስፒታል በመጓዝ ሐዘናቸውን ከመግለጽ ባሻገር፤ ወደ ትውልድ መንደሩ ለመሸኘት ተሰባስበው ነበር።

ረፋድ ላይም የድምጻዊው አስከሬን በታላቅ አጀብ ከአዲስ አበባ በመነሳት በስተ ምዕራብ 100 ኪሎ ሜትሮች ርቃ ወደምትገኘው የትውልድ ከተማው አምቦ እየተወሰደ ሳለ መንገድ ላይ ቀብሩ አዲስ አበባ መፈጸም አለበት በሚሉ ወገኖች አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ተደረገ።

በአንድ በኩል ቤተሰቡ ልጃቸው በሚኖሩበት ከተማ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እንዲፈጸም እንደሚፈልጉ ሲነገር ሌሎች ደግሞ በኖረባትና በተገደለባት አዲስ አበባ ውስጥ እንዲያርፍ የሚጠይቁ ወገኖች ነበሩ። በዚህም ቁርጥ ያለ መደምደሚያ ላይ ሳይደረስ አስከሬኑ ወደ ከተማዋ እንዲመለስ ተደረገ።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሃጫሉ የቀብር ዕለት በቴሌቪዥን ቀርበው እንደተናገሩት "አስከሬኑ ወደ ቤተሰቦቹ እየተሸኘ ሳለ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች አስከሬኑን ነጥቀው ወደ አዲስ አበባ መለሱት" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።

በተመሳሳይም የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ወደ ቤተሰቦቹ እየተወሰደ ሳለ "መንገድ በማስቀየርና በመቀማት አመጽን አዲስ አበባ ተጀምሮ አዲስ አበባ እንዲያልቅ ሲቀሰቀስ" ነበር በማለት ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ ጋር የነበረውን ክስተት ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳም "አስከሬኑ በቤተሰቡ ጥያቄ መሰረት ከጳውሎስ ሆስፒታል ወጥቶ ወደ አምቦ እየተሸኘ ሳለ፤ ከቤተሰቡ ፍቃድ ውጪ ቡራዩ ሲደርስ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደርጓል" ሲሉም ተናግረዋል።

ቢቢሲን ጨምሮ የድምጻዊው ቤተሰቦች ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃል የሃጫሉ ቀብር አምቦ ከተማ ውስጥ እንዲፈጸም እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በዚህም ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደረገው አስከሬን በኦሮሞ ባህል ማዕከል ውስጥ እንዲያርፍ ከተደረገ በኋላ በቤተሰቡ ጥያቄ መሰረት አስከሬኑ በሄሊኮፕተር ወደ አምቦ እንዲወሰድ መደረጉን ለቤተሰቡ ቅርብ የሆኑ ግለሰብ ለቢቢሲ በወቅቱ ተናግረዋል።

የኢንተርኔት መቋረጥ

ለግጭቶቹ መስፋፋትና ለጥቃቶቹ መዛመት በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ የሚሰራጩት ሐሰተኛና አባባሽ መልዕክቶችን ለመቆጣጠር ሲባል የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው ማክሰኞ ረፋዱ ላይ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት የተለመደ ድርጊት ነው በማለት የተለያዩ ወገኖች እርምጃውን ቢቃወሙትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ግን የኢንተርኔት አገልግሎት የብሔር ጥላቻን ለማስፋፋት ጥቅም ላይ በመዋሉ መንግሥት አገሪቱንና ሕዝቡን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ለማቋረጥ መገደዱን ተናግረዋል።

ባለፈው አርብ ለቢቢሲ እንደገለጹት የነበረው አለመረጋጋት በመወገዱና ተስተጓጉሎ የነበረው መደበኛ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት በመመለሱ በዚህ ሳምንት ውስጥ ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ይመለሳል ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል።

ሞት እና ውድመት

የሃጫሉ ሞት ከተሰማ በኋላ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በርካታ ሰዎች በሐዘንና በቁጣ አደባባይ ወጥተው ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ከመጋጨታቸው በተጨማሪ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲ ነገሌና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከጸጥታ አካላት ጋር በተፈጠረ ግጭትና በተፈጸመ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት ለህልፈት ተዳርጓል። በመንግሥትና በግለሰቦች ንብረትም ላይ ካባድ ውድመት እንደተፈጸመ ከየአካባቢዎቹ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ ከማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በተለያዩ ከተሞች የተፈጠረው አለመረጋጋት መልኩን ቀይሮ ማንነትን መሰረት ወዳደረጉ ጥቃቶችና ወደ ዘረፋ መሸጋገሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከፍተኛ ውድመት ያጋጠማት የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገሩት ጥቃት ፈጻሚዎቹ ክሰተቱን ለራሳቸው አላማ መጠቀሚያ ለማድረግ በተለይ ኢላማ ያደረጓቸው ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ከማክሰኞ ጀምሮ በነበሩ ጥቂት ቀናት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ ቢያንስ አስር ሰዎች ህይወታቸው የጠፋ መሆኑን ፖሊስ የገለጸ ሲሆን በተመሳሳይ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥም 11 የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ 156 ሰዎች ሞተዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነት ግርማ ገላን እንደተናገሩት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በ167 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል።

የተፈጸሙትን ጥቃቶች "ዘግናኝና አሳፋሪ የግድያ ወንጀሎች" መሆናቸውን ያመለከቱት ምክትል ኮሚሽነሩ አላማውም በማኅበረሰቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር ታስበው የተፈጸመ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እስር

የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት ምክንያት በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት በተለያዩ ስፍራዎች ለውድመት ተዳርጓል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ፖሊስ በተለያዩ ድርጊቶች ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን ግለሰቦች መያዝ የጀመረው ከማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ነበር።

በዚህም መሰረት ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የአስከሬን ሽኝት መስተጓጎልና ከአንድ የፖሊስ አባል ግድያ ጋር በተያያዘ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 35 ሰዎችን በቁጥጥር መዋላቸውን የፌደራልና እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች አስታወቀዋል።

በተጨማሪም አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ሌሎችም የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት በፖሊስ መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባና እስክንድር ነጋ ፍርድ ቤት ቀርበው ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።

ከዚህ ባሻገርም በነበሩት ተከታታይ ቀናት በተፈጸሙ ግድያዎችና የንብረት ውድመቶች ተጠረጠሩ 1084 ሰዎችን መያዙን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሲያስታውቀ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋም በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።