ፌስቡክ የዶናልድ ትራምፕን የምረጡኝ ቅስቀሳ አገደ

ፌስቡክ አንድ የዶናልድ ትራምፕን የድጋሚ ምረጡኝ ማስታወቂያ ቅስቀሳ መልእክት ከገጹ ላይ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ መልእክቱ የፌስቡክን ደንብና ሁኔታዎች ስለሚጥስ ነው ብሏል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ለቅስቀሳ የተጠቀሙበት ምልክት የናዚ ጀርመን አርማ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይህን ደግሞ ፌስቡክ ሊታገሰው የሚችለው አልሆነም፡፡

የተገለበጠ ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለውና መደቡ ቀይ የሆነው ይህ ምልክት በናዚ እንደ አርማ ካገለገለው ምልክት ጋር ተቀራራቢነት ያለው ነው፡፡

የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላት በበኩላቸው ምልክቱን የተጠቀምነው በአሜሪካ ግራ ዘመም እንቅስቃሴን እያፋፋመ ያለውን አንቲፋ የተባለውን ቡድን ለመተቸት ነበር ሲሉ ፕሬዝዳንቱን ተከላክለዋል፡፡

ፌስቡክ ግን ምንም ይሁን ምን ማስታወቂያው ጥላቻን የሚሰብክ በመሆኑ አስወግደነዋል ብሏል፡፡

ይህ የፌስቡክ እርምጃ በግዙፍ የማኅበራዊ ሚዲያ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችና በዋይት ሃውስ መካከል ያለውን ፍጥጫ ወደ አዲስ ምዕራፍ ይወስደዋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ባለፈው ወር ትዊተር ኩባንያ በተመሳሳይ ዶናልድ ትራምፕ የሚኒያፖሊሱን ክስተት ተከትሎ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ያሰፈሩት ጽሑፍ ነውጥን ያበረታታል በሚል አንስቶባቸው ነበር፡፡

ይህን የትዊተር እርምጃን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ ቁጣቸውን ገልጸው ፕሬዝዳንታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ‹ተጠያቂነትን የሚጨምር የሕግ ማጥበቂያ ሸምቀቆ› ማሰራቸው አይዘነጋም፡፡

ፌስቡክ በወቅቱ ትዊተር የወሰደውን ርምጃ በፕሬዝዳንቱ ላይ መውሰድ ነበረበት በሚል ከፍተኛ ውግዘት አስተናግዶ ነበር፡፡

አሁን ፌስቡክ የፕሬዝዳንቱን የምረጡኝ ቅስቀሳ መልእክት ማንሳቱ ዶናልድ ትራምፕን ክፉኛ እንደሚያስቆጣ ይጠበቃል፡፡

ትራምፕ ከትዊተር ይልቅ ፌስቡክን ለምርጫ ቅስቀሳ እጅግ አድርገው ይፈልጉታል፡፡

ትልቁ የፕሬዝዳንቱ የምረጡኝ ቅስቀሳ በጀት የሚፈሰውም ወደ ፌስቡክ ገጽ ነው፡፡

የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ በተነሳው ነውጥ ዙርያ ትራምፕ ‹‹ዘራፊዎችን ዘረፋ ሲጀምሩ፣ ተኩሱም ይቀጥላል›› የሚል መልእክት በትዊተርና ፌስቡክ አስፍረው ነበር፣ ያኔ፡፡

ትዊተር በወቅቱ በመልእክቱ ላይ እርምጃ ሲወስድ ፌስቡክ ቸል በማለቱ የፌስቡክ ኩባንያ ሰራተኞች ‹‹በድርጅታችን አፍረናል›› ብለው እንደነበር አይዘነጋም፡፡