ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኒውዚላንድ ከ11 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ፖሊስ ተገደለ
እጅግ ሰላማዊ በምትባለው ኒው ዚላንድ አንድ ፖሊስ መገደሉን ተከትሎ ‹‹ጉድ!›› እየተባለ ነው፡፡ ፖሊስ መደበኛ አሰሳ እያደረገ ሳለ ነበር አንድን ግለሰብ መኪናውን ሊያስቆም ሲሞክር ተተኩሶበት የሞተው፡፡
ሌላ ባልደረባው የሆነ የትራፊክ ፖሊስም ክፉኛ ቆስሏል ተብሏል፡፡
የአንድ ፖሊስ መገደል በዚያች አገር አነጋጋሪ ዜና የሆነው እንዲህ አይነት ድርጊት ከጎርጎሳውያኑ 2009 ጀምሮ ተሰምቶ ስለማያውቅ ነው፡፡
የኒውዚላንድ ፖሊስ የተለየ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር መሣሪያ አይታጠቅም፡፡ ፖሊስ በሥራ ላይ ሳለ ተገደለ ሲባልም ከ11 ዓመታት በኋላ የትናንቱ የመጀመርያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ከ11 ዓመታት ወዲህ በግንቦት 2009 የተገደለው ሌላኛው የኒውዚላንድ ፖሊስም እንዲሁ ቤት ለቤት መደበኛ አሰሳ ሲያደርግ ነበር አደጋው የደረሰበት፡፡
‹‹ሟቹን ባልደረባችንን በጸሎታችን እናስበዋለን፤ እጅግ አዝነናል›› ብለዋል የፖሊስ አዛዡ አንድሩ ኮስተር፡፡
አንድሩ ለሚዲያ እንደተናገሩት ሟቹ ፖሊስ በተሸከርካሪዎች ላይ አሰሳ በሚያደርግበት ወቅት ምንም ዓይነት መሣሪያ አልታጠቀም ነበር፡፡
በዚህ ዓመት በኒውዚላንድ ለ6 ወራት ብቻ ለልምምድ ያህል ‹‹የታጠቁ ፖሊሶች ቡድን›› ተሰማርቶ ነበር፡፡
የፖሊሶች አዛዥ አንድሩ ኮስተር ይህ ስልጠና አሁን እንዳበቃና ኒው ዚላንድ የፖሊስ ኃይሏ መሣሪያ አንጋች እንደማይሆን አረጋግጠዋል፡፡
‹‹እኛ የሕዝባችን አገልጋዮች ነን፤ ሕዝባችን ስለኛ የሚሰማው ስሜት መልካም ሆኖ እንዲቆይ እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ በኒውዚላንድ እኛ ፖሊሶች መቼም ቢሆን ጠመንጃ አናነግትም›› ብለዋል አቶ ኮስተር