በነቀምቴ አንድ የፖሊስ አባል በ'አባ ቶርቤ' በጥይት ሲገደል ሌላኛው ቆሰለ

በነቀምቴ ከተማ 'አባ ቶርቤ' በሚባለው ቡድን ሁለት የከተማው ፖሊስ አባላት ዛሬ ረቡዕ በጥይት ተመትተው የአንደኛው ህይወት አለፈ።

በፖሊሶቹ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ከቀትር በፊት ከረፋዱ አምስት ሰዓት ገደማ ላይ ሲሆን በጥይት ከተመቱት የአንደኛው የከተማዋ ፖሊስ አባል ህይወቱ ሲያልፍ ሌላኛው ደግሞ ሆስፒታል ገብቶ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኝ የነቀምቴ ከተማ ጸጥታ እና አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሚስጋኑ ወቅጋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት "በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሰዎችን በማስፈራራት ከዚያም ጥቃት በሚፈጽመው በዚህ ቡድን የከተማው ሁለት የፖሊስ አባላት በሽጉጥ ተመትዋል። አንዱ ህይወቱ ሲያልፍ አንዱ ደግሞ ቆስሎ በነቀምቴ ሆስፒታል ህክምና ላይ ይገኛል።"

ሳጅን ደበላ እና ሳጅን አዱኛ የተባሉት እነዚህ የከተማው የፖሊስ አባላት ነቀምቴ ከተማ ቀበሌ 05 በእግር እየተጓዙ ሳሉ ነበር በጥይት የተመቱት ሲሉ አቶ ሚስጋኑ ተናግረዋል። በጥቃቱም የሳጅን አዱኛ ህይወት ማለፉንም አረጋግጠዋል።

ይህ በከተማው በሚገኙ የጸጥታ አባላት ላይ የተፈጸመው ጥቃት የመጀመሪያ አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከቀናት በፊትም ግንቦት 16/2012 ዓ.ም በተመሳሳይ መልኩ በነቀምቴ ከተማ በጠራራ ፀሐይ የኮሚኒቲ ፖሊስ አባል የሆነ ግለሰብ ጫማ እያስጠረገ ሳለ በጥይት ተመቶ መገደሉን አቶ ሚስጋኑ አስታውሰዋል።

ኃላፊው እንደሚሉት ዛሬ በፖሊስ አባላቱ ላይ የተፈጸመው ግድያና ጥቃት ከቀናት በፊት በኮሚኒቲ ፖሊስ አባል ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አመልክተዋል።

"የታጠቀ እና በድብቅ የሚንቀሳቀስ ኃይል በከተማው ውስጥ አለ። ይህ ኃይል በመንግሥት አመራሮች እና የጸጥታ ኃይል አባላት ላይ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ሲያደርስና ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል" ሲሉ ክስተቱ የቆየ እንደሆነና ኢላማ ያደረገውም የመንግሥት አካላት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

'አባ ቶርቤ' ወይም ባለሳምንት የተባለው ቡድን የተለያዩ የፌስቡክ ገጾችን በመጠቀም ጥቃት እፈጽምባቸዋለሁ የሚላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በገጹ ላይ እንደሚያሰፍር አቶ ሚስጋኑ ተናግረዋል።

"የሳጀን ደበላ ስምም ከዚህ በፊት በቡድኑ የፌስቡክ ገጽ ላይ ሰፍሮ ነበር። በዚህም ምክንያት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተነግሮት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሲደረግ ነበር። ግን መቼ ይፈጸማል የሚለው ማወቅ ስለማይቻል አስቸጋሪ ነበር" ሲሉ የቡድኑን ድርጊት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ግለሰቦች የፖሊስ አባላት እንደመሆናቸው የኅብረተሰቡን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ በኅብረተሰቡ ውስጥ እየተጓዙ ሳሉ ነው ይህ ችግር ያጋጠመው" ብለዋል።

ለአንድ የፖሊስ አባልና ለሌላው ከባድ ጉዳት ምክንያት ከሆነው ጥቃት ጋር በተያይዘ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው የለም የተባለ ሲሆን ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

አባ ቶርቤ ማነው?

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ "አባ ቶርቤ ማለት የአሸባሪው ሸኔ የከተማው ክንፍ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሸኔ በጫካ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል አለው። በከተማ ደግሞ 'አባ ቶርቤ' እና 'ሶንሳ' ተብሎ የሚጠራ ቡድን አለው። እነዚህ ቡድኖች በተቻላቸው መጠን ግድያ በመፈጸም ሽብር ለመፍጠር እየሞከሩ ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ቡድኖች ጥቃት የሚያደርሱት በጠራራ ፀሐይ ከተማ መሃል ነው። ይህን መንግሥት መቆጣጠር ለምን ተሳነው? ተብለው የተጠየቁት አቶ ጅብሪል "ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ሥር የዋሉ አሉ። ለመግደለ ሲሄዱ የተገደሉም አሉ። ምንም አይነት የተለየ ስልጠናም ሆነ መሳሪያ የላቸውም። የሚጠቀሙት ሰልት የሚጠቀሙት ሰልት፤ ማህበረሰቡን በመምሰል፤ ድንገት ነው አደጋ የሚያደርሱት። ለማምለጥ በሚያመቻቸው ቦታ በድንጋት አደጋ አድርሰው ይሰወራሉ" ብለዋል አቶ ጅብሪል።

ከዚህ ቀደምም ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ታደሰ የአባ ቶርቤ አባላት ናቸው በተባሉ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።