ቻይናውያን ወላጆች የተሰረቀባቸውን ልጅ ከ32 ዓመት በኋላ አገኙ

ሲገናኙ

የፎቶው ባለመብት, CCTV

የምስሉ መግለጫ, ሊ ዢንግዚህ ከ32 ዓመት በኋላ ልጇን ስታገኝ

ቻይናውያን ጥንዶች ልጃቸውን የተሰረቁት እአአ በ1988 ሲሆን ከ32 ዓመት በኋላ ዳግም ለመገናኘት በቅተዋል።

ማኦ ዪን ልጁ የተሰረቀበት ገና የሁለት ዓመት ጨቅላ ሳለ ነበር። ያኔ አባትና ልጅ ከልጆች ማቆያ እየመጡ የነበረ ሲሆን አባት ለልጁ የሚጠጣው ለመግዛት ወደ መደብር ጎራ በማለቱ ነበር ልጁ የሌቦች እጅ ላይ የወደቀው።

እናቱ 100 ሺህ በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት በመላው ቻይና ፈለጉት።

ሰኞ እለት በአንድ የፖሊስ ጉባኤ ላይ እናትና ልጅ ተገናኝተዋል። አሁን የ34 ዓመት ወጣት የሆነው ልጅ ከዚህ በኋላ ጊዜውን ከቤተሰቦቹ ጋር ለማሳለፍ ማቀዱን ተናግሯል።

"በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የረዱንን ሰዎች ማመስገን እፈልጋለሁ" ብላለች እናት ሊ ዢንግዚህ።

ማኦ ዪን እንዴት ተሰረቀ?

እአአ የካቲት 23 1986 ነው የተወለደው፤ ሞኦ ዩን። እናቱ ለሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት በታሕሳስ ወር ላይ በሰጠችው መግለጫ " በጣም ብልህ፣ ቆንጆ እና ጤናማ" ነበር ሲሉ ያስታውሱታል።

ጥቅምት 17 1988 ማኦ ዢንጂንግ፣ አባት፣ ከህፃናት ማቆያ እያመጡት ነበር። በወቅቱ ይኖሩ የነበሩበት በሻንዢ ግዛት ዢያን ከተማ ነበር።

ያኔ ልጁ ውሃ ለመጠጣት እንደሚፈልግ ተናገረ። በሆቴል በር ላይ ቆመው አባት ቀዝቃዛ ቀወሃ ለመግዛት ገባ፤ ልጁን ሰረቅ እያደረገ እያየ ቢሆንም ልጁ በሌቦች እጅ ወደቀ-ተሰረቀ።

ቤተሰቡ ልጃቸውን በከተማዋ ፈለጉ፣ ፖስተሮች በየአካባቢው በመለጠፍ አሰሱ። በአንድ ወቅት እንዳገኙት ተሰምቷቸው ነበር፤ ነገር ግን የሐሰት መረጃ በመሆኑ ምክንያት ተስፋቸው መከነ።

ቤተሰቡ ከተገናኛ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, CCTV

የምስሉ መግለጫ, ቤተሰቡ ከተገናኛ በኋላ

እናቱ ሊ፣ ልጇን ለመፈለግ ስትል ስራዋን አቋረጠች፤ 10 ሺህ በራሪ ወረቀቶች በማዘጋጀት በ10 ግዛቶችና ከተሞች ፍለጋ አደረገች፤ ነገር ግን ፍላጎቷ ፍሬ አላፈራም።

በዓመታት ውስጥ በበርካታ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ቀርባ ልጄን ያያችሁ ስትል ተማጽናለች። እናትየው ልጇን ለማግኘት ካላት ጉጉት የተነሳ የድምፃውያን ውድድር በሚካሄድበት ኤክስ ፋክተር ላይ ሁሉ ቀርባለች።

ወደ 300 የሚሆኑ ልጅሽን አየነው፤ አገኘነው የሚሉ ጥቆማዎችን ተከትላ ባክናለች፤ ነገር ግን አንዱም አልተሳካም።

እአአ በ2007 እናት ሊ "ቤቢ ካም ባክ ሆም" (በግርድፉ ልጄ ሆይ ወደ ቤትህ ተመለስ) የሚሰኝ ድርጅት ውስጥ ሌሎች ልጆቻቸው የጠፉ እናቶችን ለመርዳት በበጎ ፈቃደኝነት ገባች።

እንደ አገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘገባ ከሆነ የእርሷን ልጅ የበላው ጅብ አልጮህ ብሎ በበጎ ፈቃደኝነት ዘመኗ 29 ሕጻናትን ወደ እናቶቻቸው እቅፍ መልሳለች።

ልጇ እንዴት ተገኘ?

ሚያዚያ ወር ላይ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ፖሊስ በሲቹአን ግዛት ስለሚገኝ አንድ ግለሰብ መረጃ ደረሰው። መረጃው ከዓመታት በፊት በማደጎ ስለተወሰደ ልጅ ይናገራል።

ይህ ግዛት ከዢያን 1000 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ነው።

ፖሊስ መረጃውን ሲፈትሽ የማደጎ ልጁ 34 ዓመት ሞልቶታል። ከዚያም ማኦ ዢንግዚ እና የሊ ዢንግዢህ ልጅ መሆኑን ለመለየት የዘረመል ፍተሻ ተደረገ። ውጤቱም ልጃቸው መሆኑን አረጋገጠ።

ማኦ ዪን እናት አባቱ ያወጡለት ስም ቢሆንም የማደጎ ወላጆቹ ጉኒንጊንግ ሲሉ ሰይመውታል።

አሁን አዳራሽ ማስዋብ ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን ስለ ወደፊቱ ሲናገርም "እርግጠኛ አይደለሁም" ቢልም ከወላጆቹ ጋር ግን ጊዜውን እንደሚያሳልፍ ተናግሯል። ፖሊስ እንዳለው በወቅቱ ህጻኑ ልጅ ለሌላቸው ቤተሰቦች በ840 ዶላር ተሸጧል።

እናት ሊ የልጇን መገኘት የሰማችው ከአስር ቀን በፊት ነው። ዕለቱ የእናቶች ቀን ነበር፤" ካገኘሁት ስጦታ ሁሉ የላቀውን ነበር የተቀበልኩት" ብላለች በወቅቱ።

በ1988 የተሰረቀው ልጅ ግን ምርመራ እስካሁን ድረስ እንደቀጠለ ነው።

በቻይና የልጆች ስርቆት ለአስርታት ችግር ሆኖ ቀጥሏል። መንግሥት ይፋዊ ቁጥር ባይኖረውም እንደ ቤቢ ካም ባክ ሆም መረጃ ከሆነ 14,893 ወንድና 7,411 ሴት ህጻናት መጥፋታቸው ተገልጾ እየተፈለጉ ነው።

በቻይና እአአ በ2015 20ሺህ ሕጻናት በየዓመቱ እንደሚሰረቁ የወጣው መረጃ ያሳያል።

በ2009 የቻይና ሕዝብ ደህንንት ሚኒስትር የዘረ መል መረጃዎችን ሰንዶ በመያዝ ከ6000 በላይ የጠፉ ህጻናትን ማግኘቱ ተነግሯል።

በግንቦት 2016 ሚኒስትሩ "የማገናኘት" መርሃ ግብር ያስተዋወቀ ሲሆን እስከ 2019 ድረስ 4000 ሕጻናት ከቤተሰባቸው ጋር እንዲገናኙ አድርጓል።