የኮሮናቫይረስ ክራሞት በኢትዮጵያ፡ ከመጋቢት እስከ ግንቦት

ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሮናቫይረስ ያለበት ሰው ከተገኘ ዛሬ ሁለት ወር ሞላው፤ በዚህ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በአጠቃለይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 261 ደርሷል።

እስካሁን ድረስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር አዲስ አበባ ከፍተኛ ሲሆን በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ 14፣ በአፋር ክልል በሚገኝ ለይቶ ማቆያ 13፣ በትግራይ ክልል ስድስት እንዲሁም በደቡብ ክልል አራት ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ ተረጋግጧል።

በተጨማሪም 106 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገግሙ ለ39 ሺህ 48 ናሙናዎች ምርመራ መደረጉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያወጡት የዕለት ሁኔታ መግለጫ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ጤና ሚንስትር ዶ/ር ሊያ እንዳሉት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው በርካታ ግለሰቦች የኮሮናቫይረስ እየተገኘባቸው ነው። ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ሳይኖራቸው ኮቪድ-19 የሚገኝባቸውም ሰዎች ቁጥር እንዲሁ ጨምሯል።

ቢቢሲ ላለፉት ሁለት ወራት የወጡትን ዕለታዊ መግለጫዎችን መለስ ብሎ ሲቃኝ በግንቦት ወር ሦስት ቀናት ብቻ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተመልክቷል።

መጋቢት- አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ የመድኒት ምርምርና የጃክ ማ ድጋፍ

ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ በግዛቷ ከማግኘቷ በፊት ከጥር 20/2012 ጀምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅትና የጥንቃቄዎች ስታደርግ እንደነበር በወቅቱ ለመገናኛ ብዙኅን ይፋ ሆኖ ነበር።

በወቅቱ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የማኅበረሰብ ጤና የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት መስጫዎችን እያቋቋሙ ነበር። ይህ ወር ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እግሩን ማስገባቱ የታወቀበት ወር ብቻ አይደለም፤ ከአዲስ አበባ ባሻገር አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ አዲስ ቅዳምም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው መጋቢት 4/2012 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ በኮቪድ-19 እንደተያዘ የተረጋገጠው ግለሰብ ጃፓናዊ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ለሥራ የመጣ መሆኑንና ከኢትዮጵያ በፊት ቡርኪናፋሶ እንደነበር ተገልጿል።

ግለሰቡ በኢትዮጵያ ቆይታው ወደ ተለያዩ ከተሞች በመጓዙ ከእርሱ ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 117 ሰዎች ተለይተው የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልፀው ነበር።

ከዚህ በኋላ መጋቢት ስድስት ከእኚህ ግለሰብ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሁለት ጃፓናውያንና አንድ ኢትዮጵያዊ በቫይረሱ መያዛቸው ተገለፀ።

መጋቢት ሰባት ከዱባይ የመጣ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ መያዙ ተጠርጥሮ ምርመራ ሲደረግለት በቫይረሱ መያዙ ስለተረጋገጠ ለይቶ ማቆያ መግባቱ የተነገረው በዕለቱ ነበር።

ከዚህ በኋላ ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ እየተረጋገጠ ወደ ለይቶ ማቆያ ይላኩ ጀመር።

የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን በቫይረሱ የተያዙ ግለሰቦች አንዱ በንክኪ ምክንያት የተጋለጠው ሲሆን ሌላኛው ከዱባይ የመጣ ግለሰብ ናቸው።

ከዚህ በኋላ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከተውጣጡ አካላት ጋር በመሰብሰብ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመግታት ይረዳል የተባሉ መመሪያዎችን ያስተላልፈዋል።

በጽህፈት ቤታቸው በኩል መጋቢት 7 2012 በዋጡት መግለጫ ትላልቅ ሕዝባዊ ስብሰባዎች መከልከላቸው፣ አነስተኛ ስብሰባዎችም ቢሆኑ ያለ ጤና ሚኒስቴር እውቅና እንዳይካሄዱ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም በስተቀር ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ የኃይማኖት ተቋማት ለአምልኮ የሚታደመውን ሰው ቁጥር እንዲቀንሱ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ መመሪያዎች የተላለፉ ሲሆን በዚሁ መግለጫ ላይ መገናኛ ብዙኀን ትክክለኛ መረጃ ለማኅበረሰቡ እንዲያደርሱ ተጠይቀዋል።

በወቅቱ ዜጎች አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ በጎ ፈቃደኞች የግንዛቤ ማስጨበጥ እንዲሰሩ ጥሪ ተላልፎ ነበር።

የመጀመሪያው በእድሜ የገፉ ሴት በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠው መጋቢት 10 ነበር። እኚህ የ85 ዓመት ሴት ከባህር ማዶ የመጡና ራሳቸውን ለይተው ጤናቸውን ሲከታተሉ የነበረ መሆኑ በወቅቱ የተገለፀ ሲሆን፤ የበሽታውን ምልክት በማሳየታቸው የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ አንድ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ላቦራቶሪ ብቻ የነበራት ሲሆን በስድስት ቀን ውስጥ መመርመር የቻለችውም 342 ናሙናዎችን ብቻ ነበር።

የኮቪድ 19 መከላከል ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በመገናኘት መጋቢት ሰባት ካሳለፏቸው ዋና ዋና ውሳኔዎች በተጨማሪ ሌሎች ውሳኔዎችን አሳለፉ።

በዚህ ውሳኔያቸውም መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች በራሳቸው ወጪ በተመረጡ ሆቴሎች ለአስራ አራት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ ተወሰነ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ሰላሳ አገራት የሚያደርገውን በረራ በጊዜያዊነት ማቆሙ የተገለፀው በዚሁ መግለጫ ላይ ነበር።

የጭፈራ እና የመጠጥ ቤቶች ቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሲባል በጊዜያዊነት እንዲዘጉ ሲወሰን፣ የተለያዩ ክልሎች ወደ ክልላቸው የሚገቡ ሆነ የሚወጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ክልከላ አስቀመጡ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚል ከመጋቢት 16 ጀምሮ ተጨማሪ ውሳኔ እስከሚተላለፍ ድረስ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲያከናውኑ ወስኗል።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 12 ለመድረስ የፈጀበት ጊዜ 10 ቀናት ብቻ ነው። በወቅቱም ለ480 ሰዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎ ነበር።

መጋቢት 18/2012 ዓ.ም ባህላዊ ህክምናን እና ሳይንሳዊ ምርምርን በማጣመር ከእጽዋት የኮሮና ቫይረስ መድኃኒት ለማግኘት ባለሙያዎች እያደረጉ ያለው ሙከራ የመጀመሪያ የቤተ ሙከራ ሂደት ማለፉ ተገለፀ።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ያገገመ አንድ ግለሰብ መኖሩ የተገለፀው መጋቢት 19/2012 ነው። መጋቢት 20/2012 ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ በኮቪድ-19 የተገኘበት ዕለት ነበር።

በወቅቱ የአንድ የቤተሰብ አባል የሆኑ ሁለት የአዳማ ነዋሪዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው መረጋገጡ ተሰምቷል።

ከዚህ በኋላ በአማራ ክልል ባህርዳርና አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዲስ ቅዳም ከተማ ውስጥ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ የመጋቢት 21 መግለጫ ያሳያል።

በማግስቱም፣ መጋቢት 22/2012 ዓ.ም፣ በድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ የሆነና ከአውስትራሊያ የመጣ ግለሰብ በቫይረሱ መያዙ ተገለፀ።

በመጋቢት ወር የአገር አቀፍ የኮሮናቫይረስ ምረመራ የሚደረገው በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የነበረ ሲሆን በዚያው በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ሁለተኛ መመርመሪያ ላብራቶር መደራጀቱ የተገለፀው ደግሞ መጋቢት 24 ነው። በተለያዩ ቦታዎችም የሚገኙ ላብራቶሪዎች ሥራ ጀመሩ።

በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል የመጀመሪያው ሞት የተመዘገበው መጋቢት 27/2012 ዓ.ም ነው። ግለሰቧ የስድሳ ዓመት አዛውንት ሲሆኑ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ለይቶ ማቆያ ህክምና ሲደረግላቸው ነበር። በዚያው ዕለት የ56 ዓመት ጎልማሳ የነበሩ ሁለተኛው ግለሰብ መሞታቸው ተሰምቷል።

በመጋቢት ወር ከፍተኛ ቁጥር ያለው በቫይረሱ የተያዘ ሰው የተመዘገበው ስምንት ሲሆን እርሱም መጋቢት 29/2012 ነበር።

በመጋቢት ወር ብቻ ኢትዮጵያ 2496 ናሙናዎችን የመረመረች ሲሆን 55 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።

ሚያዚያ ፦ አፋር፣ ጅግጅጋ፣ ትግራይ

በዚህ ወር ብቻ ወደ 28000 የሚጠጉ ናሙናዎች በተለያዩ ክልሎችና ተቋማት ውስጥ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

በሚያዚያ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ዘጠኝ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል፤ በዚሁ የመጀመሪያ ሳምንት ነው ሦስተኛ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መሞቱ የተገለፀው።

ግለሰቧ የ65 ዓመት አዛውንት የዱከም ከተማ ነዋሪ የነበሩ ሲሆን በወቅቱ ወደ ሆስፒታል የሄዱት ለሌላ ሕክምና ነበር።

ከጃክ ማ ለአፍሪካ አገራት የተሰጠው የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ቻይናውያን የጤና ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለጤና ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ ያደረጉትም በዚሁ ወር ነው።

የሚያዚያ ወር ከመጋቢት በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተመዘገበበት ሲሆን በመላው አገሪቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 100 ለመድረስ ጥቂት ቀናት ብቻ ነበር የፈጀው።

የመጋቢት ወር ሲጠናቀቅ 55 የነበረው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አድጎ ወደ 105 ለመድረስ አስር ቀናት ብቻ ናቸው የፈጁበት።

በእነዚህ ቀናት ውስጥ ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ዘጠና ናሙናዎች መመርመራቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚያዚያ ወር እንደ ሚሌኒየም አዳራሽ የመሳሰሉ ሰፋፊ ስፍራዎች ለለይቶ ማከሚያነት የተዘጋጁ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በርካታ ግለሰቦች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሃብቶች መኖሪያ ቤታቸውን፣ ሕንፃቸውን ለለይቶ ማቆያነት ሲሰጡም ተስተውሏል።

በዚህ በሚያዚያ ወር በርከት ያሉ ከጅቡቲ የተመለሱ እና በድሬዳዋ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ፣ ከፑንትላንድ በመምጣት በጅግጅግ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተገለፀ ሲሆን ሚያዝያ 14 ደግሞ አፋር ክልል ገዋኔ አካባቢ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ ተገለጿል።

በቫይረሱ የተያዘ አንድም ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይገኝ የቀረው ሚያዚያ 15/2012 ነው። በዕለቱ ለ965 ናሙናዎች ምርመራ ቢደረግም በቫይረሱ የተያዘ ግለሰብ አልተገኘም።

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ወስጥ መከሰቱ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዚ ከአንድ ሺህ በላይ (1019) ናሙናዎች መመርመራቸው የተገለፀው ሚያዚያ 17/2012 ሲሆን በወቅቱም 22 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ናሙናዎችን የመመርመር አቋሟን በማሳደግ በ24 ሰዓት ውስጥ 2016 ናሙናዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረጓ የተገለፀው በዚሁ ወር (ሚያዚያ 24 2012) ነበር።

ከፑንትላንድ በመምጣት በጅግጅግ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያለ ግለሰብ በቫይረሱ መያዙ የታወቀውም ሚያዚያ 18/2012 ዓ.ም ነው።

በዚህ ወር (ሚያዚያ 24/2012) ኢትዮጵያ በቀን 2016 ናሙናዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረጓ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ በላይ ናሙናዎች ላይ ምርመራ ባደረገችበት ዕለት (ሚያዚያ 24/2012) በቫይረሱ የተያዘ አንድም ሰው ያልተገኘ ሲሆን፣ በዚሁ ዕለት በአጠቃላይ በአገር ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 133 ደርሶ ነበር።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ከአዲስ አበባ፣ ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ አድማሱን በማስፋት ሚያዚያ 25/2012 ዓ.ም በደቡብ ክልል ስልጤ ዘን ስልጢ ወረዳ አንዲት የ45 ሴት የቤት ለቤት ቅኝትና አሰሳ ሲደረግ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ ተነግሯል።

በወቅቱ ግለሰቧ ቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳልነበራቸውና ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክም የሌላቸው መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል አራተኛዋ ግለሰብ መሞታቸው የታወቀው ሚያዚያ 27/2012 ዓ.ም ነበር።

በወቅቱ ግለሰቧ እድሜያቸው 75 መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ የነበሩት በተጓዳኝ ሕመም ታመው መሆኑ ተገልጿል።

ነገር ግን ግለሰቧ የመተንፈስ ችግር አጋጥሟቸው የነበረ ሲሆን ናሙና ተወስዶ ምርመራ እየተደረገላቸው እያለ ሕይወታቸው ማለፉ በወቅቱ በወጠዓው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

ግለሰቧ በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ነው።

በዚህ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ 17 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጾ ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበው ሚያዚያ 28/2012 ዓ.ም ሲሆን አብዛኛዎቹ ከጅቡቲ የመጡ እና በአፋር ለይቶ ማቆያ የነበሩ፣ እንዲሁም ከፑንትላንድ የመጡ እና በጅግጅግ ዩኒቨርስቲ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

በማግስቱም 29 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲገለፅ ከእነዚህ መካከል 19 ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ እንዲሁም ቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪም የሌላቸው ነበሩ።

በዚህ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በትግራይ ክልል አራት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን የመረመረች ሲሆን ቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 191 ደርሶ ነበር።

በኢትዮጵያ እስከ ሚያዚያ 30 ድረስ 194 ሰዎች ባቫይረሱ ሲያዙ ለ30306 ናሙናዎች ምርመራ ተደርጓል።

የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈው በዚህ ወር መጨረሻ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር በኮቪድ-19 መከላከል ላይ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎቸ የመድን ዋስትና እንዲገባላቸው የሚያስችል ፊርማ አከናውኗል።

ግንቦት- ወልዲያ፣ ወላይታ፣ ቡታጅራ

በግንቦት ወር ሦስት ቀናት ብቻ 56 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ፣ ከስድስት ሺህ በላይ ናሙናዎች መመርመራቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫዎች ያሳያሉ።

በግንቦት የመጀመሪያው ቀን ብቻ 2 ሺህ 383 ሰዎች በመመርመር በአገሪቱ በአጠቃላይ የተመረመሩ ናሙናዎችን ቁጥር 32 ሺህ 689 ደርሷል።

በዚሁ ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 16 ሲሆን በወቅቱ እንደተገለፀው አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 210 ደርሷል።

በዚሁ ዕለት በጽኑ የሕሙማን ክፍል የነበሩ አንድ የ65 አመት አዛውንት ሞተው በኢትዮጵያ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር አምስት የደረሰ ሲሆን በዚህ ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ ሰዎች መካከል 13 የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆኑ አንድ ከወልዲያ የለይቶ ማቆያ፣ አንድ በወላይታ ሶዶ ለይቶ ማቆያ ሌላኛው ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ መሆናቸው ተገልጿል።

በዚህ ወር በአንድ ቀን ብቻ 29 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የተገኘው ግንቦት 2/2012 ዓ.ም ነበር። ይሀም በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 239 አድርሶታል።

አንድ ግለሰብ አዳማ ከተማ በተደረገ የቤት ለቤት አሰሳ ቅኝት የተለዩ መሆናቸው ሲገለፅ፣ ሰባቱ ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 21 ደግሞ ከአዲስ አበባ ናቸው ተብሏል።

በዚህ ወር ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ከትግራይ ክልል የተገኙ ሲሆን በአጠቃለይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 250 ደርሷል። እስካሁን ድረስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር አዲስ አበባ የሚመራ ሲሆን የሶማሌ ክልል በሁለተኛነት ይከተላል።

እስካሁን ድረስ 105 ሰዎች ሲያገግሙ፣ በመላው አገሪቱ ለ36 ሺህ 624 ሰዎች ምርመራ ተደርጓል።