ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ "እናቴን በእናቶች ቀን በኮሮናቫይረስ አጣሁ"
የእናቶች ቀን ሳምንታት ሲቀሩት አያ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) ለእናቷ ስጦታ እያፈላለገች ነበር።
የ33 ዓመቷ አያ ለእናቷ ስጦታ ስትፈልግ፤ እናቷን በእናቶች ቀን እንደምታጣ ፈጽሞ አልገመተችም ነበር።
የአያ እናት ግብፅ ውስጥ ኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው የመጀመሪያዎቹ አስር ሰዎች አንዷ ነበሩ።
እስካሁን 2,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 160ው ሞተዋል።
"ላቅፍሽ እፈልጋለሁ፤ ግን አልችልም"
የአያ እናት ለሳምንት ያህል ተዳክመው ነበር። ነገር ግን በነበሩበት ሁኔታ ሕይወታቸው ያልፋል ብላ አላሰበችም።
መሞታቸውን ስትሰማ ራሷን ስታለች።
"ወንድሜ እየተሻላት ነው ብሎኝ ነበር። ድና ለልደቷ ወደ ቤት እንደምትመለስ ተስፋ አድርገን ነበር። የእናቶች ቀንና ልደቷን አጣምረን ልናከብርላት አስበን ነበር። ወንድሜ መሞቷን ሲነግረኝ ውሸትህን ነው አልኩት።"
የአያ እናት በደቡብ ካይሮ በሚገኘው ሄልዋን ግዣት ወዳለ ሆስፒታል የተወሰዱት ከህልፈታቸው አንድ ቀን በፊት ነበር። የ69 ዓመቷ እናት ከዚያ በፊት ለሳምንት ያህል በግል ህክምና መስጫ ውስጥ ነበሩ።
መጀመሪያ ባደረጉት ምርመራ ኮሮናቫይረስ 'የለብዎትም' ተብለው ነበር። ከዚያ ግን ከሁለት ቀናት በኋላ በድጋሚ ተመረመሩ።
አያ እናቷን ያዋራችው ማክሰኞ ቀን ነበር። "የዛን ቀን ከአባቴ ጋር ነበርኩ፤ እሁድ ዕለት የደም ስር ምርመራ አድርጎ ስለነበር አብሬው ነበርኩ" ትላለች።
አያ እናቷን ሳትሰናበታቸው መሞታቸው እጅግ ጎድቷታል።
ሕይወታቸው ባለፈበት ቀን በመላው ግብፅ መስጊዶች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ተላልፎ ነበር። በመስጊዶች ፀሎት ማድረግም ተከልክሎ ስለነበር የቀብር ፀሎቱን ራሷ ማድረግ ነበረባት።
የእናቷን አስክሬን ከሆስፒታል ለማውጣት ረዥም ሰዓት መጠበቅ ስለነበረባት ቀብሩ የተፈጸመው ማታ ነበር።
"ጥቂት ቤተሰብ ብቻ ነበር የተገኘው፤ ሁላችንም ጭንብል እና ጓንት አጥልቀን ነበር። የወንድሜ ሚስት እጄን ጥብቅ አድርጋ ይዛ 'ላቅፍሽ እፈልጋለሁ፤ ግን አልችልም' አለችኝ።
"የወንድሜ ሚስት እናትም በሀዘን ተሰብራ ነበር። ግን አንዳችን ሌላውን ማጽናናት አልቻልንም። አባቴም እናቴን አልተሰናበታትም። ቀብሩ ላይ ቢገኝም አንድ ሳምንት አላያትም ነበር።"
የአያ እናት ከሞቱ በኋላ አባቷም ኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸው እናቷ ይታከሙበት ወደነበረው ሆስፒታል ገብተዋል።
አባቷ አገግመው ወደ ቤት የተመለሱት ከሳምንት በፊት ነው።
አያ እና ወንድሟ ኮሮናቫይረስ ባይገኝባቸው ራሳቸውን አግልለዋል። "እንደ ቤተሰብ አንዳችን ሌላውን መደገፍ እንኳን አልቻልንም" ትላለች አያ።
"እናቴ ሰማዕት ናት"
የ31 ዓመቷ መሐንዲስ ረና ሳሜህ በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች የሚዘከሩበት የዋትስአፕ ቡድን ፈጥራለች። የሞቱት ሰዎች እንዲፀለይላቸው ስማቸው ተጽፎ ይሰራጫል።
ረና፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሞቱ ሰዎችን ስም ትሰበስባለች። ወዳጅ ዘመድ የሞተባቸው ሰዎችም ያጡትን ሰው ስም ይሰጧታል።
"ሰዎች እየሞቱ ነው። መስጊዶች ተዘግተዋል። ለእኛ ደግሞ የቀብር ሥነ ሥርዓት ትልቅ ዋጋ አለው" ትላለች።
የእስልምና አስተምሮት በቀብር ላይ ብዙ ሰዎች ሲገኙ ዋጋ አለው ይላል።
ረና የዋትስአፕ ቡድኑን እንደፈጠረችው 256 አባላት ተቀላቅለዋል። ዋትስአፕ ከዚህ በላይ ሰዎች በአንድ ቡድን እንዲሰባሰቡ ስለማይፈቅድም፤ የፌስቡክ ገፅ ተከፍቷል።
የፌስቡክ ገፁን የከፈተው የ30 ዓመቱ ነጋዴ ራሚ ሳአድ፤ በኮሮናቫይረስ በሞተ ሰው ቀብር ላይ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ፎቶግራፍ አይቶ ልቡ እንደተነካ ይናገራል። ቀድሞ መሰል ሥነ ሥርዓቶችን የሚታደሙ በርካቶች ነበሩ።
"ያየሁት ነገር ያሳዝናል፤ ስለዚህም የፌስቡክ ገፁን ከፈትኩ" ይላል።
ገፁ በአስር ቀን 4,000 ተከታይ አፍርቷል።
አያ እንደምትለው፤ የዋትስአፕ እና የፌስቡክ ገፆቹ፤ በርካታ ሰው ለሟቾች እንዲፀልይ ይረዳሉ።
"ብዙዎች በእናቴ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸውልኛል። መቼ ስለእናቴ ህልፈት እንደሰሙ እንኳን አላውቅም። አራተኛ ክፍል አብሮኝ ይማር የነበረ ልጅ ሳይቀር ደውሎልኛል።"
እንዲህ አይነት ድጋፍ ማግኘቷ እያጽናናት እንደሆነ ትናገራለች።
"እንዲህ አይነቱ ተግባር እናቴን ሰማዕት ያደርጋታል፤ የሰው ድጋፍ ብርታትም ይሰጠኛል። እንዲህ አይነት ብርቱ ሰው መሆኔን አላውቅም ነበር። እናቴ በሌላ ሁኔታ ብትሞት ኖሮ ከሀዘኑ ፈጽሞ አልተርፍም ነበር።"