የእስያ አገራት በሁለተኛ ዙር ኮሮናቫይረስ እየተጠቁ ነው

ደቡብ ኮሪያ ፣ ሴንጋፖርና ቻይና ሁለተኛ ዙር ኮሮናቫይረስ እያጠቃቸው ካሉ የእስያ አገራት መካከል ናቸው። ይህ በአገራቱ እየታየ ያለው ሁለተኛ ዙር ኮሮናቫይረስ ከውጭ የመጣ እንደሆነ ተገልጿል።

የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ቻይና እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ የመዘገበችው ምንም ዓይነት አዲስ የኮሮናቫይረስ ሕሙም የለም። ነገር ግን በቅርቡ ከውጭ ወደ ቻይና የገቡ 34 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።

ደቡብ ኮሪያም ከትናንት እስከ ዛሬ 152 አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙባት ሲሆን ከነዚህ ምን ያህሉ ከውጭ የመጡ ናቸው የሚለው አልታወቀም።

በትናንትናው እለት ሴንጋፖር ደግሞ 47 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን ከእነዚህ 33 የሚሆኑት ከውጭ የመጡ ናቸው ተብሏል።

በሌላ በኩል በቻይና ስምንት ሞት የተመዘገበ ሲሆን ሁሉም ሞቶች ኮሮናቫይረስ በተቀሰቀሰባት ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ የተመዘገቡ ናቸው።

ሶስቱም አገራት ቫይረሱን በመከላከልና ስርጭቱን በመቆጣጠር ረገድ ውጤታማ እየሆኑ የነበረ ቢሆንም ከእነዚህ አገራት ውጭ ቫይረሱ እየተሰራጨ ያለበት ፍጥነት የአገራቱን ስኬት መና እንዳያስቀረው ከፍተኛ ስጋት አለ።

አሁን ትልቁ ስጋት ያለው አውሮፓና አሜሪካ ላይ በመሆኑ ትኩረት ያለውም እነሱ ላይ ሆኗል። ነገር ግን በተጠቀሱት የእስያ አገራት ላይ እየታየ ያለው አዳዲስ ታማሚ እስያም አውሮፓና አሜሪካ ካሉበት ደረጃ ብዙ ሩቅ እንዳልሆነች የሚያሳይ ነው።

የማሌዥያ የጤና ሚኒስትር ኑር ሂሻም አብዱላ ዜጎቻቸው ከቤት ሳይወጡ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን እነዲጠብቁ ለምነዋል። ማሌዥያ በቫይረሱ 710 ሰዎች መያዛቸው ታውቋል።