ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውሮፓ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ 'ማዕከል' ሆናለች ተባለ
በቀደሙት ሳምንታት የኮሮናቫይረስ ማዕከል የነበረችው ቫይረሱ የተቀሰቀሰባት ቻይና የነበረች ሲሆን ባለፉት ጥቂት ቀናት በታየው ሁኔታ ግን አውሮፓ የቫይረሱ ማዕከል ወደ መሆን መምጣቷን የዓለም ጤና ድርጀት አስታወቀ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የአውሮፓ አገራት ቫይረሱን ተቆጣጥረው ነፍስ ለማዳን መጠነ ሰፊ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
"ይሄ እሳት እንዲነድ አትተዉት" በማለት በአውሮፓ እየታየ ያለው የኮሮናቫይረስ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢነትን ለመግለፅ ሞክረዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ ይህን ያሉት በርካታ የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን እንዲሁም ሞትን እያስመዘገቡ ባለበት በዚህ ወቅት።
ጣልያን ከአውሮፓ አገራት ከፍተኛውን የኮሮናቫይረስ ስርጭትና ሞት እያስመዘገበች ያለች የአውሮፓ አገር ነች።
ባለፈው አንድ ቀን በተወሰኑ ሰዓታት ውስጥ በጣልያን 250 ሞቶች ሲመዘገቡ እስካሁን በአጠቃላይ 1266 ሞቶች፤ 17660 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል።
ከጣልያን ቀጥሎ በቫይረሱ ክፉኛ የተመታችው የአውሮፓ አገር ስፔን ስትሆን በትናንትናው እለት ብቻ የሟቾች ቁጥር በእጥፍ ሲጨምር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 4231 ደርሷል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚያውጁ አስታውቀዋል።
በበርካታ የአውሮፓ አገራት ድንበር ላይ ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ምርመራና ቁጥጥር እየተደረገ ነው።