ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኬኒያ ወደ ሶማሊያ ሕገወጥ ደም የሚያዘዋውሩ ላይ ምርመራ ጀመረች
የኬኒያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኬኒያውያን የለገሱት ደም በሕገወጥ መልኩ ወደ ሶማሊያ ይወሰዳል በሚል የቀረበውን ቅሬታ እየመረመርኩ ነው አለ።
ምርመራው መንግሥታዊ ተቋም በሕገወጥ መልኩ የለጋሾችን ደም መሸጡን ጭምር ያካትታል ተብሏል።
በኬኒያ ብሔራዊ የደም ለጋሾች አገልግሎት መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎችንም ጭምር ያካትታል።
የኬኒያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የሆኑት ሙታኢ ካግዌ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ኬኒያ ለረዥም ዓመታት ከለጋሾች የምትሰበስበው በቂ ባለመሆኑ በደም እጥረት ተቸግራ መቆየቷ ተጠቅሷል።
የኬኒያ ደም ለጋሾች አገልግሎት ለ15 ዓመታት ሙሉ በሙሉ በአሜሪካ መንግሥት ሲደገፍ ቢቆይም ድጋፉ ግን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ተቋርጧል።
ኬኒያ በቂ የደም ክምችት እንዲኖራት ብትጥርም ሳይሳካላት የቆየ ሲሆን ለዚህም እንደምክንያት የተጠቀሰው የአሜሪካ ድጋፍ መቋረጥ እንዲሁም የኬኒያውያን ደም የመለገስ ባህል ዝቅተኛ መሆን ነው።
ባለፈው ዓመት ኬኒያ 500ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዳ ብትንቀሳቀስም ሩብ ያህሉን እንኳ መሰብሰብ ሳትችል መቅረቷ ተገልጿል።