ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከ200 ሰዎች በላይ ሞቱ
በኢራን ከ210 በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምከንያት መሞታቸውን ቢቢሲ ከተለያዩ ሆስፒታሎች ያገኘው መረጃ አሳየ።
በርካቶቹ ሟቾች ቫይረሱ በኢራን መጀመሪያ በተከሰተባቸው ሁለት ከተሞች፣ በዋና ከተማዋ ቴህራን እንዲሁም ቆም የተሰኘችው ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸው ታውቋል።
የሟቾቹ ቁጥር መንግሥት ከተናገረው በስድስት እጥፍ እንደሚልቅ ሲሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 34 ሰዎች ብቻ መሞታቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።
የጤና ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ የሆኑት ኪያኖሽ ጃሃንፑር ሚኒስቴራቸው ግልጽ መሆኑን በመናገር ቢቢሲን ሀሰተኛ መረጃ እየነዛ ነው ሲሉ ወንጅለዋል።
የቆም ከተማ የሕዝብ እንደራሴ አባል መንግሥት እውነታውን እየሸፋፈነ ነው ብለው ከወነጀሉ በኋላ አሜሪካ እውነታውን የሚያሳይ መረጃ እየተሰጠ አይደለም በማለት ስጋቷን ተናግራለች።
ማይክ ፖምፒዮ " "ለኢራን መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ጥሪ አቅርበናል" ብለዋል በትናንትናው ዕለት በዋሽንግተን በነበራቸው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ።
"የኢራን የጤና ተቋማት የሚገኙበት ሁኔታ ዘመናዊና የተደራጁ አይደሉም፤ በውስጥ እየተካሄደ ስላለውም ወቅታዊ መረጃም ማግኘት ፈታኝ ሆኗል።" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አባስ ሙሴይቭ የአሜሪካ የእርዳታ እጅ መዘርጋትን አጣጥለውታል።
"በኢራን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ድጋፍ ለማድረግ እጇን የዘረጋችው አገር፣ አገራችን ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር ማዕቀብ የጣለች፣ የኢኮኖሚ ሽብርተኝነት በማካሄድ ለሕክምና ተቋማቶቻችን እንኳ መድሃኒትና ቁሳቁስ መግዛት እንዳንችል ያደረገችው አገር መሆኗ ያሳዝናል። የፖለቲካ የሥነልቦና ጨዋታ ለመጫወት መፈለጓ ነው" ብለዋል።
ኢራን ያጋጠማትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዴት መቆጣጠር እንዳለባት ላታውቅ እንዲሁም የቫይረሱ ወረርሽኝ መጠን ልትደብቅ ትችላለች የሚል ስጋት አለ።
ቢቢሲ በኢራን ከሚገኙ ሆስፒታሎች እስከ ሐሙስ ዕለት ድረስ በሰበሰበው መረጃ መሰረት እስካሁን 210 ሰዎች መሞታቸውን መረዳት ችሏል።
በኢራን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሳይቀሩ በቫይረሱ መያዛቸው የተሰማ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ህሙማን የሚገኙትም ቴህራን መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
አርብ ዕለት የሚካሄድ የፀሎት ስነስርዓት የተከለከለ ሲሆን ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ዝግ ሆነው ውለዋል።
ከኢራን የሚወጡም ሆነ ወደ ኢራን የሚገቡ በርካታ በረራዎች በመከልከላቸው በርካቶች በያሉበት ለመቆየት ተገድደዋል።