ከፋ ዞን፡ በቦንጋ ሠርግ አስደግሶ "የሙሽራዬ ቤት ጠፋኝ" ያለው ግለሰብ የእስር ጊዜውን አጠናቀቀ

በደቡብ ክልል፤ ከፋ ዞን፤ ቦንጋ ከተማ ሠርግ አስደግሶ "የሙሽራዬ ቤት ጠፋኝ" ያለው ግለሰብ ከእስር መለቀቁን የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ክፍሌ ተካ ለቢቢሲ ገለፁ።

ነገሩ እንዲህ ነው. . .

ግለሰቡ በቦንጋ ከተማ ቤት ተከራይቶ ይኖር ነበር። ዕድሜው አሁን ወደ 30 ይጠጋል። የኑሮ ሁኔታውም ዝቅተኛ ደረጃ የሚባል ዓይነት ነው ይላሉ የሚያውቁት።

ታዲያ አንድ ቀን ለሠፈሩ ሰዎች "ላገባ ነው" ሲል ያበስራቸዋል። መቼም አንድ ሰው በሕይወቱ ወደ መልካም ምዕራፍ ሲሸጋገር ደስ ያሰኛልና እነርሱም ደስታቸውን ይገልፃሉ። "አበጀህ የእኛ ልጅ" ይሉታል።

ሁሉም ባቅሙ እያዋጣ እርሱም ካመጣው ጋር እየተጨማመረ ድግሱ በትብብር ተዘጋጀ።

የሠርጉ ቀን ሲደርስም ሸራ ተወጥሮ፣ ወንበር ተሰባስቦ ለእንግዶች ተሰናዳ። ዳሱም በአበባ እና በዘንባባ ተጌጠ። ጎረቤቱም እንደ ባህሉ ተሰባስቦ በአቅማቸው ድግሱን ሲያስተናብሩ ዋሉ።

ሁሉም ተሰናድቶ ካለቀ በኋላ ሙሽራው ከአጃቢዎቹ ጋር [6 ወንድ እና ሁለት ሴት] እየጨፈሩ፣ እየዘፈኑ ሙሽሪትን ለማምጣት ዴቻ ወረዳ፤ ሻፓ ወደ የሚባል ቀበሌ አመሩ።

ሻፓ በእግር ቢያንስ 1 ሰዓት ይወስዳል። ሚዜዎቹና አጃቢዎቹ "ደስታህ ደስታችን ነው" ብለው ይህንን ሁሉ ርቀት ተጉዘው ሥፍራው ደረሱ።

ይሁን እንጂ ሙሽራው አንዳች ነገር እንደጠፋው ሁሉ መንደሩን መዟዟር ጀመረ። በድካም የዛሉት ሚዜዎቹ "ቤቱ አንደርስም ወይ? ሙሽራዋ የታለች?" ብለው መጠየቃቸው አልቀረም። ግን መዳረሻው አልታወቅ አለ። በአካባቢው የሚታይም ሆነ የሚሰማ የሠርግ ሁናቴ የለም።

ግራ የተጋቡት አጃቢዎች "የታለች?" ሲሉ ሙሽራውን ወጥረው ይይዙታል።

"ልጅቷ ያለችበት ቤት ጠፋብኝ " ይላቸዋል። 'ሙሽራዋ ጠፋች'።

በነገሩ ግራ የተጋቡት አጃቢዎቹ የሚያደርጉት መላ ቅጡ ጠፋቸው። ዳስ ውስጥ ሆነው እየዘፈኑ ሙሽራዋን የሚጠባበቁት ሠርገኞች ፊት እንዴት ባዶ እጃቸውን እንደሚገቡ ጭንቅ ያዛቸው።

በዚህ መሃል አንድ ሃሳብ ብልጭ አለላቸው። ከአጃቢዎቹ አንዱን ጫማው እንዲያወልቅ አድርገው በነጠላ በመሸፋፈን ሙሽራ አስመስለው እየዘፈኑ፣ እየጨፈሩ ይዘው መግባት። በሃሳቡ ተስማሙ፤ እንዳሰቡት አደረጉ።

ቤቱ እንደደረሱም "በእግሯ ረዥም ሰዓት ስለተጓዘች በጣም ደክሟታል።" ብለው ወደ ጫጉላው ቤት አዝለው ያስገቧታል። የሆነውን ማንም የገመተ የለም።

ትንሽ ቆይቶ "ሙሽራዋ ትውጣና ራት ይበላ" ሲሉ ደጋሽ ጎረቤቶች ይጠይቃሉ። ምላሹ አሁንም "ደክሟታል" የሚል ነበር።

አቶ ሙሉጌታ ገ/ሚካኤል ሠርግ ተጠርተው ከተገኙት ጎረቤቶች መካከል አንዱ ነበሩ።

"ከሌላ ቦታ መጥቶ እኛ ሠፈር ቤት ተከራይቶ ይኖር ነበር። 'ላገባ ነው' ብሎ የተወሰኑ ጎረቤቶቹን ሠርግ ጠራ። እኔም ተጠርቼ ስለነበር ሠርጉ ላይ ተገኘሁ። ሙሽራዋን እንቀባለለን ብለን ሽር ጉድ ስንል ዋልን። በ'ጂ ፓስ' የሠርግ ሙዚቃ ተከፍቶ እየተጠባበቅን ነበር።

በኋላ ላይ አምሽተው መጡ። ነገር ግን ብንጠብቅ ብንጠብቅ ሙሽራዋ አትመጣም። ወሬ አይቀርምና ሴት አስመስለው ይዘው የገቡት ወንድ ነው ተባለ። እንግዶችም ድግሱን ሳይቀምሱ ወዲያው ነበር በብስጭትና በእፍረት የተበታተኑት" ሲሉ አጋጣሚውን ያስታውሱታል።

ሚስጢሩ ከጫጉላ ቤቱ ወጥቶ ወደ ዳሱ ሲዛመት ግን አፍታም አልቆየ። "ሴት አይደለም ወንድ ነው" የሚል። 'ጉድ' ተባለ። የሆነውን ባለማመን እያጉመተመቱ ወደየመጡበት የሄዱ እንዳሉ ሁሉ ጉዳዩን ለሕግ አካል ለማሳወቅም ያሰቡ አልጠፉም።

ለፖሊስ ጥቆማ ተሰጠ። ፖሊስም በሥፍራው ተገኝቶ 'ሙሽራውን' በቁጥጥር ሥር አዋለ።

" እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር ሰምቼም አላውቅም።" የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ በአካባቢው ባህል መሠረት በሠርግ ወቅት ገንዘብ ስለሚሰጥ ግለሰቡ ይህን ያደረገው ገንዘብ ለማግኘት መሆኑን የተረዳነው በኋላ ነው ይላሉ።

ቆይተው እንደሰሙትም ሠርጉን ለመደገስ ያልተበደራቸው የጉልት ነጋዴዎች አልነበሩም።

ድርጊቱ የአገሬውን ሰው ጉድ ያሰኘ ነበር። ድርጊቱንም እጅግ ኮነኑት፤ "ለዚህ ነው ወይ ደፋ ቀና ያልነው" ሲሉ ተፀፀቱ። የግለሰቡን ፍርድም በጉጉት መጠባበቅ ያዙ።

በወቅቱ ወንጀሉን ሲከታተሉ የነበሩት የቦንጋ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ክፍሌ ተካ እንደነገሩን ግለሰቡ ሠርጉን የሠረገው ጥቃቅን ወጪዎች ሳይቀሩ ተበድሮ ነው። ሽንኩርቱም፣ እንጀራውም፣ ጠላውም ሁሉም ለድግስ የሚያስፈልጉ ነገሮች።

የተበደረውም ከተለያዩ ቦታዎችና ሰዎች ስለነበር ማንም የጠረጠረ አልነበረም።

"'ከእጮኛዬ ጋር ለመጋባት ባለሁበት ቀበሌ ጨርሼ መጣሁ' ብሎ ጓደኞቹን ሰብስቦ ሲናገር በየዋህነት አመኑት፤ ደስም አላቸው። እንደዚህ አንሸዋዳለን ብሎ ግን ያሰበ አልነበረም" ይላሉ ኮማንደር ክፍሌ።

ኮማንደር ክፍሌ፤ ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ውሎ በምርመራው ሂደት ሲጠየቅ "አጭቻት ነበር፤ ከተስማማች በኋላ ቤቷ ጠፋኝ" የሚል መልስ እንደሰጠ ይናገራሉ።

"ለትዳር ያጫሃትን ሴት ቤት እንዴት ነው አጣሁት የምትለው?" ሲሉ ጥያቄያቸውን ማስከተላቸው ግን አልቀረም።

እሱም "ወደ ቦታው ሄድን፤ ጨለማ ነው፤ ቤቱ ጠፋብኝ። ተመልሼ ባዶ እጄን ወደ ቤት ለመግባት ስለተቸገርኩ እና ድግስ የጠራኋቸው ሰዎች አታለለን እንዳይሉ ብየ፤ ወንዱን ሴት አስመስዬ በጨለማ አስገባሁ" ሲል ምላሽ መስጠቱን ኮማንደር ክፍሌ ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ ሴት ሙሽራ መስሎ የተወነውን ሠርገኛ ስምም "አላውቅም' ሲል መልስ ሰጥቷል።

እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ ሰምተውም ሆነ አጋጥሟቸው እንደማያውቅ የሚናገሩት ኮማንደር ክፍሌ፤ በሁኔታው እጅግ ተደንቀን ነበር ይላሉ።

"ሠርግ ማለት ትልቅ፣ ባህልም ወግም ነው፤ ስለዚህ የኅብረተሰቡን ባህልና ወግ ሊያበላሽ የሚችል እንደሆነ በማሰብ ነው ትኩረት ሰጥተን የተከታተልነው" ይላሉ።

በዚህም መሠረት በማጭበርበር ወንጀል ክስ ተመስርቶበት የቦንጋ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጥር 20 ቀን 2008 ዓ.ም 6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት አስተላለፈበት።

ሴት ሙሽራ መስሎ የገባው ግለሰብን ግን በተባባሪነት ለመክሰስ ጥረት ቢደረግም የግለሰቡን ማንነት ማኅበረሰቡ ሊያጋልጥ ባለመቻሉ እንዲሁም ዋናው ተከሳሽም አላውቀውም በማለቱ ማንነቱ ሳይታወቅ ቀርቷል።

ግለሰቡ የተረጋጋ ሕይወት እንዳልነበረው ኮማንደር ክፍሌ አክለዋል።

ይህ የሆነው በደቡብ ክልል፤ ከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነው ሲሆን 'የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ'ም ታህሳስ 9 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር የተካሄደው።