መንግሥት ለዜጎች መፀዳጃ ቤት እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት የተገደደባት የአፍሪካ ምድር

በቅርቡ የአንዲት ሃገር ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግሥት ለዜጎች በየቦታው መፀዳጃ ቤት ያቅርብ ሲል በይኗል።

ነገሩ የሆነው ኬንያ ውስጥ ነው። ዜጎች መፀዳጃ ቤት ማግኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው እንደሆነ ተገልጦላቸዋል። ወጪ ሸፋኙ ደግሞ መንግሥት።

ኬንያዊው ጆሴፍ ኡሩንጉ፤ ሃገሬ ውስጥ በመኪና ክፍለ ሃገራትን ማቋረጥ እኔ አልመክርም ይላል። ዋነኛው ስጋቱ ደግሞ ሞት ነው። በጎርጎሳውያን አቆጣጠር በ2018 ብቻ 3400 ሰዎች የኬንያ መንገዶች ሲሳይ ሆነው እንደወጡ ቀርተዋል።

ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ከፍጥነት ልክ በላይ ማሽከርከርና በእንቅልፍ ልብ ማሽከርከር ለመንገድ ትራፊክ አደጋዎች ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።

«ይህን ሁሉ ችለው፤ ሞት አምልጠው በመኪና ቢጓጓዙ እንኳ የመንገዶቹ ምቾት አልባነት ሌላ ጭንቀት ነው» ይላል ልምድ ያስተማረው ጆሴፍ።

እርግጥ ነው የኬንያ መንገዶች ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻሉ ነው። ምንም እንኳ አንዳንድ መንገዶች ዝናብ ሲነካቸው ቢሰረጉዱም።

«የእንግሊዝ ቅኝ ተገዥ የነበርን እንደመሆናችን በግራ በኩል ነው የምናሽከረክረው። ነገር ግን ሰዎች የተበሳሱ አስፋልቶችን ፍራቻ በስተቀኝ በኩል ሲነዱ ማየት ብርቅ አይደለም። መሃል ናይሮቢ የሚገኘው ማዕከላዊ የንግድ ቀጣና እንኳ በተሳሱ አስፋልቶች የተሞላ ነው።»

ከአደጋውና ከመንገዶቹ ምቾት ነሺነት ሌላ ኬንያ ውስጥ ክፍለ ሃገራትን በመኪና ማቋረጥ ከባድ የሚያደርገው የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ ነው።

እስከ ገደፉ የሞላ የሕዝብ ማመለሻ ውስጥ ሆነው ሽንትዎ ቢመጣስ? ኧረ ምን ሽንት ብቻ. . . ጆሴፍ ባለሥልጣናት መንገዶችን ሲያስገነቡ ስለ መፀዳጃ ቤቶች ጭራሽ አላሰቡም ሲል ይወቅሳል።

«የሕዝብ ማመለሻ አውቶብስ ሾፌሮች ድንገት ያሻቸው ቦታ ያቆማሉ። ከዚያ ሰዉ ወዳገኘው ጥሻ ጠጋ ብሎ ተንፈስ ይላል። እንደው ግድ ስለሆነ እንጂ ሴቶችም፣ ወንዶችም ሆኑ ሕፃናት በዚህ መልኩ ሲፀዳዱ ማየት ደስ አያሰኝም።»

በሚድያና ኮሚዩኒኬሽን መስክ ሥልጠና የሚሰጠው ጆሴፍ በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ በምትገኘው የሞምባሳ ከተማ ሥልጠና ሲሰጥ ተማሪዎች የነገሩትን አይዘነጋም።

«አጋጣሚ ሆኖ ተማሪዎቹ ከሞምባሳ ወደ ሌላ ቦታ በመኪና እየተጓዙ ነበር። አንድ ቦታ ቆመው የተገኘውን ይቀማምሳሉ። ታድያ ምግቡ ሰላም አልሰጣቸውም። ሾፌሩ ጥሻ ባገኘ ቁጥር እያቆመ የተማሪዎቹን የተፈጥሮ ጥሪ ሲያስተናግድ ውሎ እንደምንም ወደ መዳረሻቸው ደረሱ። እንደውም አንዱ ተማሪ በሕይወቴ እንደዚህ ዓይነት ረጅም ጉዞ አጋጥሞኝ አያውቅም ሲል አጫውቶኛል።»

የመንገድ ዳር መፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ ያስጨነቀው አንድ ኬንያዊ ታድያ ጥሻ ፍለጋውን አቋርጦ መንግሥትን ከሷል።

አድርያን ካሞቶ ጄንጋ የተሰኘው ይህ ግለሰብ መንገድ በመገንባት እጃቸው ያለበት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መፀዳጃ ቤቶችን አልገነቡም፤ ይህ ደግሞ የዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብት ነው ሲል ተሟግቷል።

የኬንያ ክፍለ ሃገራት ገዢዎች ምክር ቤትና የመንገድ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለው እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ ከረሙ።

ከሳሹን መፀዳጃ ቤት ማቅረብ እንዴት ሆኖ ነው ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሚሆነው ሲሉ ሞገቱ።

ከሳሽም ሰዎች ያለ ፍላጎታቸው ሜዳ ለሜዳና ጥሻ ውስጥ ለመፀዳዳት መቀመጣቸው ሰብዓዊነታቸውን የሚያወርድ ነው ተከራከረ።

ዓለማዊ ሕግና መፅሐፍ ቅዱስ እያጣቀሰ አቤት አለ። አልፎም ሰዎች የተፈጥሮ ግዴታቸውን በጊዜው መወጣት ሲገባቸው መንግሥት ቦታ ባለማዘጋጀቱ ምክንያት እየተሰቃዩ ነው አለ።

በስተመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ተመልክቶ ከሳሽ እውነት አላቸው ሲል ብይን ሰጠ። አልፎም መንግሥት መፀዳጃ ቤቶችን ለዜጎች እንዲያመቻች ሲል አዘዘ።

ኬንያውያን አሁን 'የሕገ-መንግሥታዊውን ሽንት ቤት' መገንባት በጉጉት እየጠበቁ ነው። እስከዚያው ግን ጥሻ ሥር ሲፀዳዱ የተመለከቱ የዱር እንስሳት ሳይታዘቧቸው የሚቀሩ አይመስልም።